የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ እና ቀጣናው ዘርፈ ብዙ ትሩፋቶችን የሚያስገኝ ነው - አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ - ኢዜአ አማርኛ
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ እና ቀጣናው ዘርፈ ብዙ ትሩፋቶችን የሚያስገኝ ነው - አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 4/2017 (ኢዜአ)፦ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከኢነርጂ ባሻገር ለኢትዮጵያ እና ቀጣናው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን የሚያስገኝ መሆኑን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ ገለጹ።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በኢትዮጵያ ያለውን የኢነርጂ አቅርቦት በከፍተኛ ደረጃ የሚያሳድግ መሆኑን ገልጸዋል።
ግድቡ የኢነርጂ ጥያቄን በመመለስ የዜጎችን ህይወት የመቀየር ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።
የሕዳሴ ግድቡ የሚያመነጨው ንጹህ እና ታዳሽ ኃይል መሆኑን ጠቅሰው፤ ከአካባቢ ጥበቃ አንጻር ያለው ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል።
ሕዳሴ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ልማት እና የእያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ ዜጋ ህይወት በመቀየር ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበርክት ጠቅሰዋል።
ግድቡ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብት የልማት መብቷን ከጋራ ተጠቃሚነት ጋር በማሰናሰን መገንባቷን አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ የትኛውንም የተፋሰሱን ሀገራት የመጉዳት ፍላጎት የላትም ያሉት አምባሳደሩ፤ የሀገሪቷ ፍላጎት በትብብር እና በመግባባት በጋራ መልማት እንደሆነም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያን ያላካተቱት የቅኝ ግዛት ዘመን ውሎች ጊዜያቸው ያለፈባቸው እና ትርጉም አልባ መሆናቸው ጠቅሰው፤ ሕዳሴ ግድብ ከዚህ አንጻር በተፋሰሱ ሀገራት አዲስ የትብብር ምዕራፍ እንደሚከፍት ነው ያስረዱት።
ኢትዮጵያ ሰላማዊ የትብብር አማራጮችን ብቻ ተጠቅማ ግዙፍ ሀገራዊ ህልሞቿን ለማሳካት መስራቷን ትቀጥላለችም ብለዋል አምባሳደሩ።