ቀጥታ፡

አፍሪካውያን ለአህጉራቸው ሰላም እና ብልጽግና ያላቸውን ቁርጠኝነት ዳግም ሊያረጋግጡ ይገባል - መሐሙድ አሊ ዩሱፍ 

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 4/2017(ኢዜአ)፦ አፍሪካውያን ለአህጉራቸው ሰላም እና ብልጽግና ያላቸውን ቁርጠኝነት በማጽናት የተሻለ መጻኢ ጊዜን ለመፍጠር በጋራ እንዲሰሩ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር  መሐሙድ አሊ ዩሱፍ ጥሪ አቀረቡ። 

የአፍሪካ ህብረት ቀን ዛሬ እየተከበረ ይገኛል። 

ቀኑ የአፍሪካ ህብረት እ.አ.አ ሴፕቴምበር 9/1999 በሲርት ድንጋጌ አማካኝነት የተቋቋመበት ቀን የሚታወስበት ነው።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ  ቀኑን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት አፍሪካውያን ቀኑን ሲዘክሩ የአህጉሪቷን ለውጦች በማክበር እና ለአንድነት፣ ሰላምና ብልጽግና ያላቸውን ቁርጠኝነት ዳግም በማረጋገጥ ሊሆን እንደሚገባ ገልጸዋል።

የህብረቱ መመስረት ውሳኔ ለአፍሪካ ትብብር፣ ትስስር እና አጋርነት መሰረት የጣለ ነው ብለዋል። 

የአፍሪካ ህብረት ቀን የጋራ ጉዟችንን፣ የህዝባችንን አይበገሬነት እና ያጋመደንን የፓን አፍሪካኒዝም መንፈስ የምናከብርበት ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ሊቀ መንበሩ በመልዕክታቸው በአፍሪካ በተለያዩ መስኮች የተመዘገቡ ስኬቶችን አንስተዋል።

በሰላምና ደህንነት፣ የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና፣ የታዳሽ ኃይል ልማት፣ ዲጂታል ኢኖቬሽንና የወጣቶችን አቅም በመገንባት የተከናወኑ ስራዎች አፍሪካን በዓለም መድረክ ያላት ሚና እንዲያድግ አስተዋጽኦ ማድረጉን ነው ሊቀ መንበሩ የገለጹት።

የአፍሪካ ህብረት ለአጋርነት፣ ትስስር እና ዘላቂ ልማት ያለውን ቁርጠኝነት ጠቅሰው መንግስታት፣ ሲቪክ ማህበረሰቡ፣ የግሉ ዘርፍ እና ወጣቱ ፈተናዎችን በጋራ በመሻገር አጀንዳ 2063 ይዞ የመጣችውን እድሎች እንዲጠቀም ጥሪ አቅርበዋል።

ሁሉም አፍሪካውያን ክብራቸው ተጠብቆ የሚኖሩባት እና መጻኢ ጊዜያቸው ብሩህ የሆነች አህጉር እጅ ለእጅ በመያያዝ እንገንባ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም