ኢትዮጵያ የማንሠራራት ጉዞና የብስራት ዘመን ላይ ትገኛለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የማንሠራራት ጉዞና የብስራት ዘመን ላይ ትገኛለች
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 4/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የማንሠራራት ጉዞና የብስራት ዘመን ላይ እንደምትገኝ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የካቢኔ ጉዳዮችና ሴክተሮች ክትትል ሚኒስትር ዴኤታ አክሊሉ ታደሰ ገለጹ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስተባባሪነት እና በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ትብብር የጳጉሜን 4 ቀን 2017 ዓ.ም የማንሠራራት ቀን "ዘላቂ ልማት ለሀገራዊ ማንሠራራት" በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የካቢኔ ጉዳዮችና ሴክተሮች ክትትል ሚኒስትር ዴኤታ አክሊሉ ታደሰ፤ በለውጡ ዓመታት ኢትዮጵያን ከቁልቁለት ጉዞ ወደ ከፍታ ያሸጋገሩ ስኬቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።
የኢትዮጵያን ገናና ሀገርነት የሚመልስ ታሪክ ሰሪና ድል አብሳሪ ትውልድ መኖሩን ጠቁመው፤ ዛሬ የተመረቀው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ህያው ምስክር መሆኑን ገልጸዋል።
በማንሠራራት ቀን የኢትዮጵያውያንን የመቻል ውጤት ለዓለም በማብሰር የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን የሀገረ መንግስት ግንባታ አስተሳሳሪ የጸና ምሰሶ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የቁልቁለት ጉዞ ዛሬ ተቋጭታል ያሉት አቶ አክሊሉ፤ ዕለቱም በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ስኬት ሀገር ማንሰራራት የጀመረችበት ጊዜ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የጀመረችውን የማንሠራራት ጉዞ ሁሉም ዜጋ በፅናት በመቆም ለባንዳና ለባዕዳን የጋራ ጠላቶች መልዕክት ማስተላልፍ እንደሚኖርበትም አስገንዝበዋል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ(ዶ/ር)፥ የማንሠራራት ቀን በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ምረቃ ዕለት መካሄዱ ለኢትዮጵያና ወዳጆቿ ድርብ ድል ነው ብለዋል።
በለውጡ ዓመታት በውሃ ሃብት አስተዳደርና ልማት እንዲሁም በኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነት የዜጎችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ያስቻሉ ተጨባጭ ስኬቶች እንደተመዘገቡም አስታውቀዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብም የኢትዮጵያን ዕድገት የሚያሳልጥ የዘመናት ቁጭትን ምላሽ የሰጠ የኅብረ ብሔራዊ አንድነት ማህተም መሆኑን ገልጸዋል።
የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵውያን ትልቅ ትርጉም ያለው የማንሠራራት ዘመን መገለጫ ነው ብለዋል።
የአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ዲፕሎማሲ ማዕከል በሆነችው አዲስ አበባ የተከናወኑ የልማት ስራዎችም የኢትዮጵያ የማንሰራራት ዘመን መሰረት መሆናቸውን አስረድተዋል።
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ሄለን ደበበ፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በማንሰራራት ቀን ለምረቃ መብቃቱ የማይዘነጋ ልዩ የታሪክ አጋጣሚ እንደሆነ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ከ70 በላይ ከተሞች የሚከናወኑ የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማቶች ዜጎች ጤናማ የኑሮ ከባቢ እንዲያገኙ ያስቻለ የማንሠራራት ዘመን መሰረት መሆኑን ተናግረዋል።
የአዋሽ ቤዚን አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አደን አቡዱ፤ የወንዞች ዳርቻ ልማት የውሃ ጤናማነትን ለመጠበቅ ጉልህ ፋይዳ አለው ብለዋል።
በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የዕቅድና ሪፎርም ዳይሬክተር ትዕግስት ዘለቀ እንደገለጹት፤ የመዲናዋ የልማት ስራዎች ቀጣዩ ትውልድ የተሻለ ሀገር እንዲረከብ የሚያደርግ የማንሠራራት መሰረት ናቸው።
የማንሠራራት ቀንን አስመልክቶ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ቅጥር ግቢ የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ምረቃ የቀጥታ ስርጭት ብስራትና በመዲናዋ የወንዝ ዳርቻ ልማት የጉብኝት መርሃ ግብር ተካሂዷል።