የህዳሴ ግድብ ለምረቃ መብቃቱ የጋራ ስኬታችን ማሳያ እና የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጊዜ ያረጋገጠ ነው-የመቀሌ እና የሽረ እንዳስላሴ ከተሞች ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የህዳሴ ግድብ ለምረቃ መብቃቱ የጋራ ስኬታችን ማሳያ እና የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጊዜ ያረጋገጠ ነው-የመቀሌ እና የሽረ እንዳስላሴ ከተሞች ነዋሪዎች
መቀሌ፣ ሽሬ፤ ጳጉሜን 4/2017 (ኢዜአ)፡- የህዳሴ ግድብ ለምረቃ መብቃቱ የጋራ ስኬታችን ማሳያ እና የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጊዜ ያረጋገጠ ነው ሲሉ የመቀሌ እና የሽረ እንዳስላሴ ከተሞች ነዋሪዎች ተናገሩ።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከ14 ዓመታት የግንባታ ሂደት በኋላ ተጠናቆ ለምርቃት መብቃቱን ተከትሎ በተለያዩ አካባቢዎች ዜጎች ደስታቸውን ገልጸዋል።
የግድቡን ምረቃ ተከትሎ የኢዜአ ሪፖርተር በትግራይ ክልል መቀሌና ሽረ እንዳስላሴ ከተሞች ተዘዋውሮ ነዋሪዎችን አነጋግሯል።
የከተሞቹ ነዋሪዎች ከረጅም ዓመታት እልህ አስጨራሽ የግንባታ ሂደት በኋላ ግድቡ ለስኬት በመብቃቱ ከፍተኛ ደስታ የተሰማቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ከመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ ፀጋይ ሃዱሽ እና መምህር ፀጋው ታደሰ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ገንዘቡን፣ ጉልበቱንና እና እውቀቱን በጋራ ያስተባበረበት ህዳሴ ግድብ ለምረቃ በመብቃቱ ደስታችን ወደር የለውም ብለዋል።
የህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለጎረቤት አገራትም ጭምር ብርሃን የሚሰጥ ታላቅ ፕሮጀክት በመሆኑ የተሳሰረ ልማትና የጋራ እድገትን የሚያመጣ መሆኑንም ገልጸዋል።
ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማጠናቀቅ መቻል ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶችንም ለማሳካት የሚያስችል እውቀት የተገኘበትና የመስራት አቅም የካበተበት መሆኑንም አንስተዋል።
ከሽረ እንዳስላሰ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ ገብረመድህን ገብረመስቀል እና ወይዘሮ ሸዊት ደስታ፤ የዛሬው እለት ለመላ ኢትዮጵያዊያን የደስታ ቀን መሆኑን አንስተው ለስኬት በመብቃቱ ደስታና ኩራት ተሰምቶናል ብለዋል።
የግድቡ መጠናቀቅ ከብርሃን ምንጭነቱም ባለፈ የህብረ ብሄራዊ አንድነታችን ማሳያ፣ የፍቅር፣ የሰላም፣ የልማትና የአብሮነት መገለጫ መሆኑን ተናግረዋል።
"ኢትዮጵያውያን እንደጀመርነው እንጨርሰዋለን" ባልነው መሰረት አሳክተነዋል እንኳን ደስ ያለን በማለት መልእክታቸውን ያስተላለፉት ደግሞ አቶ ገብረ እግዚአብሄር ገብረ ማርያም ናቸው።