የዓባይ የዘመናት የቁጭት ግዜ አልፎ የብርሃን ምንጭ ስለሆነልን ተደስተናል- የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የዓባይ የዘመናት የቁጭት ግዜ አልፎ የብርሃን ምንጭ ስለሆነልን ተደስተናል- የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች
ሀዋሳ፤ ጳጉሜ 4/2017 (ኢዜአ) :- የዓባይ የዘመናት የቁጭት ጊዜ አልፎ የብርሃን ምንጭ ስለሆነልን ተደስተናል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቆ የተለያዩ አገራት መሪዎችና ዲፕሎማቶች በተገኙበት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) መመረቁን ተከትሎ ኢትዮጵያዊያን በየአካባቢያቸው ደስታቸውን በተለያዩ መንገዶች ገልጸዋል።
በሲዳማ ክልል ሀዋሳ ከተማም የግድቡን ምረቃ ተከትሎ ነዋሪዎች በጎዳና እና አደባባዮች ላይ በመውጣት ደስታቸውን የገለጹ ሲሆን በስፍራው የተገኘው የኢዜአ ሪፖርተርም የተወሰኑትን አነጋግሯል።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል አቶ አሸናፊ ሃይሌና ወጣት አቡሌ ወንድሙ፤ የዛሬው ቀን ለመላ ኢትዮጵያዊያን የደስታና የሀሴት ቀን ሆኖ መዋሉን አንስተው፣ ዓባይ ተገድቦ መብራት ሆኖ፣ ዓሳ አብልቶና መዝናኛ ሆኖ ኢትዮጵያዊያንን ለማኖር መዘጋጀቱ ለሁላችንም አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በመሆኑም የዓባይ የዘመናት ቁጭትና የወቀሳ ጊዜ አልፎ የብርሃን ምንጭ ስለሆነልን ተደስተናል ሲሉ አስተያየት ሰጭዎቹ ገልጸዋል።
ሌሎች አስተያየት ሰጭዎች አቶ ላዕላጉ ኡሳሞ እና መሪጌታ ፈቃዱ ገብሩ፤ መላ ኢትዮጵያዊያን በገንዘብ፣ በጉልበትና በመስዋዕትነት ጭምር ዋጋ የከፈሉለት ዓባይ ተጠናቆ ለምረቃ በመብቃቱ ተደስተናል ብለዋል።
የግድቡ ግንባታ በአንድነት ቆመንና በፅናት አልፈን ያሳካነው በመሆኑ ለስኬት ሲበቃ በእጅጉ ተደስተናል ያሉት ደግሞ አቶ ወንድማገኝ ፀጋዬ እና ወጣት በቃሉ መሠረት ናቸው።
የሲዳማ ክልል ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ታምሩ ታፌ፤ የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞ የሚያፋጥንና በዚህ ትውልድ የተፃፈ ሌላ የታሪክ አሻራ መሆኑን አንስተዋል።