ኢትዮጵያ እና አልጄሪያ በንግድና ኢንቨስትመንት ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር ቁርጠኝነታቸውን ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና አልጄሪያ በንግድና ኢንቨስትመንት ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር ቁርጠኝነታቸውን ገለጹ
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 4/2017 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና አልጄሪያ በዲፕሎማሲው መስክ ያላቸውን የረጅም ጊዜ ትብብር በንግድና ኢንቨስትመንት መስክም ይበልጥ ለማጠናከር በጋራ እንደሚሰሩ አስታወቁ።
በአልጀርስ የኢትዮጵያ ኤምባሲ እና በአልጄሪያ የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ትብብር የተዘጋጀው የኢትዮጵያና አልጄሪያ የቢዝነስ ፎረም ዛሬ በአልጀርስ ከተማ ተካሂዷል።
የቢዝነስ ፎረሙ በአልጄሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደር አምባሳደር ሙክታር መሐመድ እንዲሁም የአልጄሪያ ንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ካሜል ሃሚኒ ተገኝተዋል።
ፎረሙ በአልጄሪያ ከተካሄደው አራተኛ የአፍሪካ የንግድ ትርኢት ጎን ጎን የተከናወነ ነው።
በአልጄሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሙክታር መሐመድ ኢትዮጵያ ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ያስመረቀችበት ቀን በመሆኑ ለመላው ኢትዮጵያውያንና አፍሪካውያን የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ኢትዮጵያና አልጄሪያ ለረጅም ዓመታት የዘለቀ ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ እና ፖለቲካዊ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን አምባሳደር ሙክታር ለኢዜአ ገልጸዋል።
ሁለቱ ሀገራት በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ መተባበር የሚያስችላቸውን ዕምቅ አቅም በመጠቀም በኢኮኖሚያዊ ትብብር አመርቂ ውጤት ለማስመዝገብ ጠንካራ ስራ መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
አክለውም ኢትዮጵያ የቡና፣ የሥጋ፣ የቅባትና ጥራጥሬ እህሎች እንዲሁም ሌሎች የወጪ ገበያ ምርቶችን ለአልጄሪያ ገበያ ማቅረብ የሚያስችል ትልቅ አቅም እንዳላት አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ረገድም ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ ያላት ሀገር መሆኗን በማንሳት የአልጄሪያ የቢዝነስ ድርጅቶች ከዚህ መልካም አጋጣሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።
የአልጄሪያ ንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ካሜል ሃሚኒ በበኩላቸው የኢትዮጵያና የአልጄሪያ የቢዝነስ ድርጅቶችና ግለሰቦች በጋራ መስራት የሚያስችላቸው ትልቅ ዕድል ያላት ሀገር መሆኗን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የቢዝነስ ድርጅቶችና ግለሰቦች የዚህ መልካም አጋጣሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑም ጥሪ አቅርበዋል።
በመቀጠልም በቢዝነስ ፎረሙ ላይ ኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ረገድ ያላትን ምቹ ከባቢ አስመልክቶ ማብራሪያ ተሰጥቷል።
በቢዝነስ ፎረሙ መድረክ ላይ ከኢትዮጵያ የመጣው የቢዝነስ ልዑክ አባላት ምርትና አገልግሎታቸውን ያስተዋወቁ ሲሆን በተመሳሳይም በአልጄሪያ ወገን በቢዝነስ ፎረሙ ላይ ተሳትፎ ያደረጉ የቢዝነስ ድርጅቶችና ግለሰቦችም ምርትና አገልግሎታቸውን አስተዋውቀዋል።
በቢዝነስ ፎረሙ ላይ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በአልጄሪያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ዲፕሎማቶች፣ ከንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር እና ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተውጣጡ ከፍተኛ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።
እንዲሁም በቡና፣ በቅባት እህሎች፣ በስጋ፣ በጥራጥሬ፣ በቆዳ እና የቆዳ ውጤቶች፣ በአበባ እና ሌሎች በርካታ የወጪ ንግድ ዘርፍ የተሰማሩ ከ35 በላይ የንግድ ድርጅቶች እና ላኪዎች እንዲሁም በንግድ ትውውቅ የሚሰሩ ተቋማት መሪዎችን ጨምሮ በአጠቃላይ ከ60 በላይ ተሳታፊዎች ታድመዋል።
በቀጣይ ኢትዮጵያ እና አልጄሪያ በመካከላቸው ያለውን የንግድ ልውውጥ የሚያሳድጉ የሁለትዮሽ የጋራ ቢዝነስ ፎረሞች እና የምርት እና አገልግሎት ትርዒቶች ለማዘጋጀት የጋራ ስምምነት ላይ ደርሰዋል።