ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለቀጣናዊ ትብብርና ብልጽግና ታሪካዊ እድል ፈጥሯል - ያዕቆብ አርሳኖ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለቀጣናዊ ትብብርና ብልጽግና ታሪካዊ እድል ፈጥሯል - ያዕቆብ አርሳኖ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 4/2017(ኢዜአ)፦ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለቀጣናዊ ትብብርና ብልጽግና ታሪካዊ እድልን የፈጠረ መሆኑን የውሃ ባለሙያው እና በተለያዩ ዓለም አቀፍ የውሃ ድርድሮች ላይ የተሳተፉት ያዕቆብ አርሳኖ(ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ዛሬ ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መርቀዋል።
የውሃ ባለሙያው እና በኢትዮጵያ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርድሮች ላይ የተሳተፉት ያዕቆብ አርሳኖ(ዶ/ር) የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን የኢነርጂ ፍላጎት የሚሞላና ብሄራዊ እድገትን የሚያሳልጥ መሆኑን ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።
ለቤቶች፣ ለኢንዱስትሪዎች፣ ለአገልግሎት ዘርፉ እና አጠቃላይ ለሀገራዊ የልማት ስራዎች ያለው ፋይዳ ወሳኝ መሆኑንም አብራርተዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በናይል ተፋሰስ ላይ ያለው አዎንታዊ ሚና ከፍተኛ መሆኑንም አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት ኢነርጂ እየሸጠች መሆኑን ጠቅሰው ከዚህም አንጻር ግድቡ ለቀጣናዊ ትስስር ያለው ፋይዳ ቁልፍ መሆኑን አንስተዋል።
የኤሌክትሪክ ኃይሉ ለሀገራት መተማመንን በመፍጠር፣ ትስስርን በማጠናከርና መግባባትን በማጎልበት በኩል አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የጋራ ሀብቶች ሰላም፣ መረጋጋት እና የጋራ ብልጽግናን የማረጋገጥ አቅማቸውን በከፍተኛ ደረጃ አጉልቶ የሚያሳይ እንደሆነም ነው ያስረዱት።
በተጨማሪም ግድቡ በግብርና ልማት፣ በመሰረተ ልማት ግንባታ እና በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ላይ ተምሳሌታዊ የትብብር ማዕቀፍ ተደርጎ የሚወሰድ መሆኑን ተናግረዋል።
ሀገራት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በተሞክሮነት በመያዝ በቀጣይ ቀጣናውን የሚቀይሩ ፕሮጀክቶችን በጋራ ማልማት እንዳለባቸውም ነው ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ የመከሩት።