ቀጥታ፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የትውልዱ ዳግማዊ ዓድዋ ነው

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 4/2017(ኢዜአ)፦ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የትውልዱ ዳግማዊ ዓድዋ ነው ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

በኢትዮጵያዊያን ገንዘብ፣ የላብ እና የደም ጠብታ እውን የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተጠናቆ ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተመርቋል።

የሕዳሴ ግድብ ተጠናቆ ለምረቃ መብቃቱን አስመልክቶ ኢዜአ በአዲስ አበባ ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እንደገለጹት፤ የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ለኢትዮጵያ ትልቅ ስኬት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ብዙ መስዋትነት የተከፈለበት፣ መላ ኢትዮጵያዊያን አሻራቸውን ያስቀመጡበት እና ለፍፃሜው ሲጓጉለት የነበረው ግድብ ግንባታው ተጠናቆ ለምረቃ በመብቃቱ መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡

የመዲናዋ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ታደለች ዲባባ ፤ ግድቡ ከተጀመረ ጀምሮ ቦንድ በመግዛት ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውንና አሁን ላይ ግድቡ እውን በመሆኑ የተሰማቸውን ደስታ ተናግረዋል፡፡

ሌላኛው አስተያየት ሰጭ አቶ ሽኩሪ አደም በበኩሉ፤ የሕዳሴ ግድብን እውን ለማድረግ ቦንድ በመግዛት፣ በሃሳብና በጉልበት የበኩሉን አስተዋጽኦ ሲወጣ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

ሌላው አስተያየት ሰጭ አቶ ሲሳይ ተፈራ የሕዳሴ ግድብ ታሪክ አንዱ አካል መሆን በመቻሉ መደሰታቸውን በመግለጽ፤ የግድቡ እውን መሆን ታሪክ መስራት እንደሚቻል የተረጋገጠበት ነው ብሏል፡፡

በግድቡ ግንባታ ሂደት ውስጥ በተለያየ መልኩ ድጋፎችን ሲያደርግ መቆየቱን በመግለጽ፤ የዘመናት ቁጭት የሆነው የሕዳሴ ግድብ እውን ሆኖ በማየቱ መደሰቱን የገለጹት ደግሞ አቶ ስዩም ጽጌ ናቸው፡፡፡

አቶ ግርማ ወልደጊዮርጊስ በበኩላቸው ፕሮጀክት የትውልዱ ዳግማዊ ዓድዋ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ መስከረም ኪዳኔ በበኩላቸው፤ የግድቡ ግንባታ ከተበሰረበት ጊዜ አንስቶ ድጋፍ ማድረጋቸውን በመግለጽ ፤ግድቡ ተጠናቆ በመመረቁ መደሰታቸውን ተናግራለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም