ስለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ምረቃ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ምን አሉ? - ኢዜአ አማርኛ
ስለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ምረቃ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ምን አሉ?

የህብረ-ብሔራዊ አንድነት መገለጫ የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቆ ለምረቃ መብቃቱ የበርካታ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንን ትኩረትን መሳብ ችሏል።
ከሮይተርስ እስከ አሶሺየትድ ፕሬስ፣ ከቢቢሲ እስከ አልጀዚራ ያሉ ታላላቅ መገናኛ ብዙሃን የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ምረቃን በልዩ ትኩረት ዘግበውታል።
የአንድነትና የሉዓላዊነት ተምሳሌት፦
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫነት ባለፈ የኢትዮጵያውያንን አንድነት፣ ኩራት እና የሉዓላዊነት መገለጫ መሆኑን በርካታ መገናኛ ብዙኃን በዘገባዎቻቸው አስነብበዋል።
ዶቼ ቬለ ግድቡ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያውያን ገንዘብ እና ጉልበት ያለ የውጭ እርዳታ መገንባቱን በማስታወስ ኢትዮጵያውያንን በሙሉ ልብ ያስተሳሰረ ታላቅ ፕሮጀክት ሲል መስክሮለታል።
በግድቡ ግንባታ ወቅት የታየው ህዝባዊ ተሳትፎ በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይወሰን በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ያካተተ መሆኑን የአሜሪካው ሲቢኤስ ኒውስ አስነብቧል።
ሁሉም ኢትዮጵያዊ ቦንድ በመግዛትና በልዩ ልዩ መዋጮ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረጉን ጠቅሷል።
ይህ ህዝባዊ ተሳትፎ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጭምር እንደ አርአያ የሚወሰድ ነው ሲል ገልፆታል።
ኢትዮጵያ በራሷ አቅም የገነባችው ግዙፍ ግድብ ከተዕፅኖ በፀዳ መልኩ የመልማት መብቷን ያረጋገጠ ነው።
የኢኮኖሚ እድገትና የብልጽግና መሰረት፦
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ እድገትና ብልጽግና መሰረት የጣለ መሆኑም ተዘግቧል፡፡
ሮይተርስ በዘገባው በአፍሪካ ትልቁ ኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ ግድብ መሆኑን ጠቅሶ የኢትዮጵያን የኤሌክትሪክ አቅርቦት በእጥፍ እንደሚያሳድገው አስነብቧል።
ፍራንስ-24 በበኩሉ "ኢትዮጵያ ሚሊዮኖችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ የሚያደርገውን ግዙፍ ግድብ ገንብታ አጠናቀቀች" ሲል አስነብቧል።
በሌላ በኩል ኤቢሲ ኒዉስ በኢትዮጵያ ውስጥ የኤሌክትሪክ ሀይል ተጠቃሚው ህዝብ 54% ብቻ መሆኑን ጠቅሶ ከ5ሺህ 150 ሜጋ ዋት በላይ ኃይል የሚያመነጨው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ሀይል ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ያለውን ፋይዳ አሳይቷል።
የታዳሽ ኃይል አቅርቦት ለኢንዱስትሪ መስፋፋት፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራና ለህዝቡ የኑሮ ደረጃ መሻሻል ወሳኝ መሆኑም አስታውሷል።
አሶሺየትድ ፕሬስ በበኩሉ "ኢትዮጵያውያን ተስፋን የሰነቁበት በአፍሪካ ግዙፍ ግድብ ተገንብቶ ተጠናቀቀ" ሲል የኢትዮጵያውያንን ተስፋ አንጸባርቋል።
የቀጣናዊ ትብብር ማሳያ፦
ዘገባዎቹ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድቡ ጠቀሜታ በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን ለአካባቢው ሀገራት ያለውን ፋይዳም አመላክተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ግድቡ ለጎረቤት ሀገራት ስጋት ሳይሆን የጋራ እድል መሆኑን መናገራቸውን በማሳያነት በመጥቀስ ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት ኃይል በመሸጥ ቀጣናውን በኃይል ማስተሳሰር እንደሚያስችላት ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች ግድቡን ከግዙፍነቱና ከሚያመነጨው ኃይል ባለፈ የኢትዮጵያውያንን አንድነት፣ አቅም እና ሉዓላዊነት ማሳያ አድርገው አቅርበውታል።
ቢቢሲ "የኢትዮጵያውያን ኩራት" በማለት ሲገልጸው፣ ዴይሊ ኔሽን በበኩሉ "የኢትዮጵያውያን የአዲስ ዓመት ስጦታ" በማለት ከመጭው አዲስ አመት ጋር አያይዞ ዘግቦታል፡፡