ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የአየር ንብረት ፋይናንስ መፍትሔን በራስ አቅም መፍጠር እንደሚቻል አሳይቷል -የዓለም አቀፍ ተቋማት አመራሮች - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የአየር ንብረት ፋይናንስ መፍትሔን በራስ አቅም መፍጠር እንደሚቻል አሳይቷል -የዓለም አቀፍ ተቋማት አመራሮች

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 4/2017(ኢዜአ)፦ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የአየር ንብረት ፋይናንስ መፍትሔን በራስ አቅም መፍጠር እንደሚቻል ያሳየ የአፍሪካ ፕሮጀክት መሆኑን የዓለም አቀፍ ተቋማት አመራሮች ገለጹ፡፡
ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ "ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት መፍትሄዎችን ማፋጠን፣ የአፍሪካን አረንጓዴ ልማት በፋይናንስ መደገፍ" በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል መካሄደ ከጀመረ ሁለተኛ ቀኑን ይዟል፡፡
አፍሪካ ወደ ከባቢ አየር በካይ ጋዝ በመልቀቅ ከአራት በመቶ በታች ድርሻ ቢኖራትም ከፍተኛውን የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ጉዳት ታስተናግዳለች፡፡
ከፍተኛ የበካይ ጋዝ የሚለቁ ያደጉ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥ ፋይናንስን መሸፈን አለባቸው በሚል እሳቤ የፓሪስ ስምምነትን ጨምሮ የተለያዩ ውሳኔዎች ቢተላለፉም እስካሁን ከዚህ ግባ የሚባል ውጤት አልተገኘም፡፡
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን የአፍሪካ የአየር ንብረት ፖሊሲ ማዕከል አስተባባሪ ጀምስ ሙሮምበድዚ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዓይነተ ብዙ ፋይዳ ያለው ፕሮጀክት ነው፡፡
ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ለአየር ንብረት ፋይናንስ ችግር የራስን መፍትሔ ማበጀት የሚያስችል አዲስ የፋይናንስ ሞዴል መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ከዚህም ባለፈ ኢትዮጵያ የጎረቤት ሀገራትን በታዳሽ ኃይል በማስተሳሰር ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ በመገንባት በአፍሪካ ቀዳሚ እንደሚያደርጋት ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርና በታዳሽ ኃይል ልማት ያስመዘገበችው ስኬት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ማስተማሪያ እንደሚሆንም አንስተዋል፡፡
የዓለም የእርሻና ምግብ ድርጅት ረዳት ዳይሬክተር ጀነራል እና የአፍሪካ ተጠሪ አበበ ኃይለገብርኤል (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከተባበርን ተዓምር እንደምንሰራ የተማርንበት የመቻል ምልክት ነው ብለዋል፡፡
ትራንስፖርት፣ ንግድና ኢንቨስትመንት፣ ግብርና ሜካናይዜሽን፣ ቴክኖሎጂና ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶች ከኃይል ጋር የተሳሰሩ መሆናቸውን ገልጸው፤ ለአየር ንብረት ለውጥ መፍትሔ እንደሚሆን ጠቅሰዋል፡፡
ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ታዳሽ ኃይል በማምረት የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ከመከላከል ባለፈ የአየር ንብረት ፋይናንስ ምንጭ ሆኖ ያገለግላል ነው ያሉት፡፡
የአየር ንብረት ለውጥ ፋይናንስ ከበለጸጉ ሀገራት መምጣት አለበት የሚለው ውጤት እንዳላመጣ በመጥቀስ፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የአየር ንብረት ፋይናንስን በራስ አቅም ማመንጨት እንደሚቻል ለሌሎችም ትምህርት የሰጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡