ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መሰል ፕሮጀክቶችን በራስ አቅም ማሳካት እንደሚቻል ማሳያ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መሰል ፕሮጀክቶችን በራስ አቅም ማሳካት እንደሚቻል ማሳያ ነው
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 4/2017(ኢዜአ)፦ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መሰል ፕሮጀክቶችን በራስ አቅም ማሳካት እንደሚቻል ማሳያ ነው ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለፁ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያውያን በራሳቸው አቅም የገነቡትን ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በዛሬው ዕለት በይፋ መርቀዋል።
አስተያየት ሰጪዎቹ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በኢትዮጵያውያን አቅም ተገንብቶ ለምረቃ በመብቃቱ ደስታቸውን ገልፀዋል።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ወይዘሮ ለሊሴ ቶሎሳ ህዳሴ ግድብ ለምርቃት መብቃቱ ታላቅ ድል መሆኑን ተናግራለች፡፡
እሷም የታሪኩ አካል በመሆኗ ራሷንን እድለኛ አድርጋ እንደምትቆጥር ነው የገለፀችው።
ትንሽ ትልቅ ሳይል በሁሉም ኢትዮጵያዊ ትብብር በራስ አቅም የተጠናቀቀ ፕሮጀክት በመሆኑ ትልቅ ኩራትና ደስታ እንደተሰማት ጠቅሳለች።
የግድቡ ለምረቃት መብቃት ዜጎች ለአንድ ግብ ከተባበርን ብሄራዊ ጥቅማችንን ከማረጋገጥ ወደ ኋላ የሚጎትተን ነገር እንደሌለ ያረጋገጥንበት ነው ሲሉ የተናገሩት ደግሞ አቶ በላቸው ሃይሌ ናቸው።
ኢትዮጵያዊያን በአንድነት በመቆማቸው የግድቡን ግንባታ በራስ ሀብትና አቅም ማጠናቀቅ ችለዋል ሲሉም ተናግረዋል።
አቶ ተክለሃይማኖት ዋሚ በበኩላቸው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በርካታ ውጣ ውረዶችንና ፈተናዎችን አልፎ ለምረቃ በመብቃቱ መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡
አስተያየት ሰጪዎቹ ግድቡ ከተጀመረ ጀምሮ በገንዘብና በጉልበት እንዲሁም ቦንድ በመግዛት ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡
ሻምበል ገላዬ ጆሃር የተባሉ አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው አባቶቻችን በአድዋ ድል ያሳኩትን ጀግንነት የአሁኑ ትውልድ የሕዳሴ ግድብን በማጠናቀቅ መድገሙን አንስተዋል።
ኢትዮጵያውያን ልዩነታቸውን ጌጥ አድርገው በአንድነት ሲንቀሳቀሱ ትልቅ ድል ማስመዝገብ እንደሚችሉ በተግባር ያሳየ ፕሮጀክት መሆኑንም ተናግረዋል።
አስተያየት ሰጪዎቹ አሁን ላይ የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት መጠናቀቅ ለኢትዮጵያ ትልቅ ብስራት መሆኑን ገልፀው፤ ለወደፊትም መሰል ፕሮጀክቶችን ለማሳካት ትምህርት የሚሰጥና አቅም የሚፈጥር መሆኑንም ተናግረዋል።