ቀጥታ፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለጎረቤት ሀገራት የታዳሽ ኃይል ፍላጎትን ለማሟላት ጉልህ ሚና አለው

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 4/2017 (ኢዜአ)፡- ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ ከራሷ አልፎ ለጎረቤት ሀገራት የታዳሽ ኃይል ፍላጎትን ለማሟላት ለምታደርገው ጥረት ጉልህ ሚና እንዳለው የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ስዩም መኮንን ገለጹ።

በአዲስ አበባ ትናንት የተጀመረው ሁለተኛው የአፍሪካ አየር ንብረት ጉባኤ ዛሬም ቀጥሎ በአፍሪካ የታዳሽ ኃይል ልማትን ማፋጠን ላይ ያተኮረ ውይይት ተደርጓል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ስዩም መኮንን ኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል አማራጮችን ለማስፋት እያደረገች ስላለው ጥረት አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን በዘላቂነት ለመከላከል የታዳሽ ኃይል አማራጮችን አሟጣ ለመጠቀም በቁርጠኝነት እየሰራች ነው ብለዋል።

ዛሬ የተመረቀው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከ5 ሺህ በላይ ሜጋ ዋት ታዳሽ ኃይል በማመንጨት ከኢትዮጵያ ባለፈ የጎረቤት ሀገራትን የኃይል ፍላጎት ለሟሟላት ጉልህ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

ከውሃ ኃይል ባለፈ የንፋስ፣ የፀሐይና የእንፋሎት ታዳሽ የኃይል አማራጮችን በመጠቀም የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ለማስፋትና የዜጎችን ኑሮ ለመቀየር እየተሰራ ነው ብለዋል።

የኬንያ የአየር ንብረት ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር አሊ መሃሙድ ኢትዮጵያ የገነባችው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለአፍሪካ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት መስፋፋት ትልቅ አበርክቶ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

የኃይል አቅርቦት ለአፍሪካ ልማት የጀርባ አጥንት መሆኑን ጠቅሰው፣ የታዳሽ ኃይል አማራጮችን በማስፋት የኢንዱስትሪዎችን ምርታማነት ማሳደግና የዜጎቿን ኑሮ የማሻሻል ሥራ መጠናከር እንዳለበት ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም