ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ብሔራዊ ፕሮጀክት ብቻ ሳይሆን የፓን አፍሪካ ግልጽ አቋም ነው - ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ብሔራዊ ፕሮጀክት ብቻ ሳይሆን የፓን አፍሪካ ግልጽ አቋም ነው - ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 4/2017(ኢዜአ)፦ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ብሔራዊ ፕሮጀክት ብቻ ሳይሆን የፓን አፍሪካ ግልጽ አቋም ነው ሲሉ የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ተናገሩ።
የኬንያ ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ምረቃ በዓል ላይ ተገኝተው ለኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ስኬታማ መሆን የኢትዮጵያና የአፍሪካ ታላቅ ድል ነው ብለዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የምህንድስና ምኞት ብቻ ሳይሆን አፍሪካ የራሷን ዕጣ ፈንታ የመቅረፅ ብቃት እንዳላት የሚያሳይ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
አህጉሪቱ ሀብቷን የማስተዳደርና ብልፅግናዋን የሚያሳኩ ወሳኝ መሠረተ ልማቶችን የማቅረብ አቅም እንዳላት በተጨባጭ ያስመሰከረ መሆኑንም ተናግረዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ብሔራዊ ፕሮጀክት ብቻ አይደለም ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ የአፍሪካን ዕጣ ፈንታ በራስ አቅም የመወሰን የፓን አፍሪካ ግልጽ አቋም ማሳያ መሆኑን አስረድተዋል።
ግድቡ የአፍሪካውያንን የመሠረተ ልማት ፍላጎት በራስ አቅም የማሳካት ምሳሌ መሆኑን በመጥቀስ፤ ከአፍሪካ ኅብረት የአህጉራዊ የኃይል ትስስር ራዕይ ጋር የሚስማማ ነው ብለዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የቀጣናው የኃይል ቋት መሆኑን ያነሱት ፕሬዝዳንቱ፤ በዚህ ወሳኝ ወቅት የአፍሪካ ቀንድ እና የተፋሰሱ ሀገራት ዘላቂ የወንድማማችነት፣ የትብብር እና የጋራ ራዕይን ለማሳካት ተግተን እንሰራለን ነው ያሉት።
ለዚህም ኬንያ የምስራቅ አፍሪካ የኤሌክትሪክ ኃይል ወሳኝ ማዕከል ከሆነችው ኢትዮጵያ ጋር ትብብሯን አጠናክራ እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል።
ኬንያ ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል በመግዛት ትስስር መፍጠሯን አስታውሰው፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከሚያመነጨው ኃይል ለመግዛት ንግግሮች እየተደረጉ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በመላው አፍሪካ ተመሳሳይ ፕሮጀክቶችን ለማስፋት መነሻ የሆነ እና የአህጉሪቱን የኃይል አቅርቦት እጥረት ለመሙላት ትልቅ አቅም መሆኑን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አስደናቂ ሥራ እየሠሩ መሆኑን ያነሱት ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ማሳካታቸው የህዝቦቻችንን ምኞትና ተስፋ በትጋታችን እውን የማድረግ ሁነኛ ምሳሌ ናቸው ብለዋል።