በታላቁ ህዳሴ ግድብ የተጎናጸፍነውን ድልና ታሪክ ሠላምን በማጽናትና በሌሎች ልማቶች ሊደገም ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በታላቁ ህዳሴ ግድብ የተጎናጸፍነውን ድልና ታሪክ ሠላምን በማጽናትና በሌሎች ልማቶች ሊደገም ይገባል
አዳማ፤ ጳጉሜ 4 / 2017 (ኢዜአ)፡-በታላቁ ህዳሴ ግድብ የተጎናጸፍነውን ድልና ታሪክ ሠላምን በማጽናትና በሌሎች ልማቶች ሊደገም እንደሚገባ ተገለጸ።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቁን ተከትሎ በአዳማ ከተማ የድጋፍ ሠልፍ ተካሂዷል።
በድጋፍ ሰልፉ ላይ የተገኙት በብልጽግና ፓርቲ የአዳማ ከተማ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሸናፊ አጀማ ግድቡ የአንድነት አርማና የአብሮነት መገለጫ ነው።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ መላው የከተማው ነዋሪና አስተዳድሩ ሀብት በማሰባሰብ የላቀ ተሳትፎ ማድረጉን አስታውሰዋል።
በተለይ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የአንድነት ተምሳሌትና የአይቻልም መንፈስና የማሸነፍ መገለጫ በመሆኑ ሠላማችንን በማጽናት በሌሎች የልማት ስራዎች ለመድገም መረባረብ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በድጋፍ ሠልፉ ላይ የተገኙት የአዳማ ከተማ አስተዳደር ዋና ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ሸዋዬ ደቻሳ በሰጡት አስተያየት የግድቡ መጠናቀቅ ጥቅሙ ብዙ በመሆኑ ወደር የሌለው ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል።
የአዳማ ከተማ የሀገር ሽማግሌ አቶ ፈይሳ መገርሳ በበኩላቸው ልጅ አዋቂ ሳይል በተደረገ ተሳትፎ ግድቡ መጠናቀቅ በመቻሉ ታላቅ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል።
ሌላኛው የሰልፉ ተሳታፊና የአዳማ ከተማ ነዋሪ ወጣት ጌታሁን አበበ፤ የህዳሴ ግድብ የክብራችን መገለጫ በመሆኑ ደስታውን ለመግለጽ አደባባይ መውጣቱን ተናግሯል።