ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አህጉራዊ ትብብርና ግንኙነትን ያጠናክራል - የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሃሙድ - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አህጉራዊ ትብብርና ግንኙነትን ያጠናክራል - የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሃሙድ
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 4/2017(ኢዜአ)፦ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አህጉራዊ ትብብርና ግንኙነትን የሚያጠናክር የወንድማማችነት ምልክት ነው ሲሉ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሃሙድ ገለጹ።
በኢትዮጵያውያን ገንዘብ፣ የላብ እና የደም ጠብታ እውን የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተጠናቆ ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ተመርቋል።
የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሃሙድ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ምረቃ በዓል ላይ ተገኝተው የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የዛሬ ቀን ለሁላችንም ታሪካዊ ቀን ነው ሁላችንም የጋራ ተጠቃሚ በምንሆንበት በጋራ ጉዳያችን ላይ በመገኘታችን ክብር ይሰማናል፥ እድለኞች ነንም ብለዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለእኛ እንደ አንድ ፕሮጀክት ሳይሆን ሀላፊነትን የምንጋራበት ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ አፍሪካውያን ከተባበርን ስኬችን ማገኘት የምንችልበት ነው ብለዋል።
የላይኛውና የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት መበልጸግ የሚችሉት በጋራ እንደ አንድ ማህበረሰብ በመስራት መሆኑን ገልጸው፤ ውሃና ሌሎች ተፈጥሯዊ ሀብቶች በድንበር የተወሰኑ ሳይሆኑ የወደፊት እጣ ፈንታችንን የሚያስተሳስሩ ናቸው ሲሉም ገልጸዋል።
በአፍሪካ ስለልማት ስናወራ በውድድር መንፈስ ሳይሆን በትብብር መሆን አለበት ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው።
ሁላችንም የምንፈልገውን ብልጽግና እና ሰላምን ለማረጋገጥ ትብብር የግድ መሆኑን ገልጸው፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አህጉራዊ ትብብርና ግንኙነትን የሚያጠናክር የወንድማማችነት ምልክት ነው ብለዋል።