የግድቡ መመረቅ የኢትዮጵያ ማንሰራራት ጅማሮን ያበሰረ ነው - የቦንጋ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የግድቡ መመረቅ የኢትዮጵያ ማንሰራራት ጅማሮን ያበሰረ ነው - የቦንጋ ከተማ ነዋሪዎች
ቦንጋ፤ ጳጉሜን 4/2017(ኢዜአ)፡-ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተጠናቆ መመረቅ የኢትዮጵያ ማንሰራራት ጅማሮን ያበሰረ ነው ሲሉ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የቦንጋ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
የግድቡ መመረቅ ከፈጠረባቸው ከፍተኛ ደስታ በተጨማሪ ለልማት የሚያደርጉትን አስተዋጾ ለማጠናከር እንዳነሳሳቸው ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያውያን የተባበረ ክንድና በመንግስት ብርቱ ጥረት የተገነባው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከ14 ዓመታት እልህ አስጨራሽ ፈተናዎች በኋላ ዛሬ ተጠናቆ ለምረቃ በቅቷል
የግድቡ መመረቅን በማስመልከት አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የቦንጋ ከተማ ነዋሪዎች ግድቡ ኢትዮጵያ የማንሰራራት ጉዞ መጀመሯን ማሳያ ነው ብለዋል።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል በከተማው በኤሌክትሮኒክስ ንግድ ሥራ ላይ የተሰማራው ወጣት እንግዳወርቅ አለሙ፣ የዛሬው ቀን ታሪካዊና ልዩ ከመሆኑ በላይ ዳግም የተወለድኩ ያክል ትልቅ ደስታ ነው የተሰማኝ ብሏል።
ያለፈው ትውልድ በአድዋ ድል የሀገርን ሉአላዊነት በማስጠበቅ ታሪክ ሰርቷል፤ የአሁኑ ትውልድ ደግሞ የዘመናት ቁጭት የነበረውን የዓባይ ወንዝ ገንብቶ በማጠናቀቅ የራሱን አሻራ አሳርፏል በማለትም ስሜቱን በደስታ ገልጿል።
ለሕዳሴው ግድብ በ8100-A እና በተደጋጋሚ ቦንድ በመግዛት አሻራውን ማሳረፉን የገለፀው ወጣቱ፣ በአብሮነት ከቆምን ከዚህም በላይ መስራት እንደምንችል የሕዳሴው ግድብ ማረጋገጫ ነው ብሏል።
በርካታ ፈተናዎችን በማለፍ ግድቡ ዛሬ ለምረቃ በመብቃቱ መደሰታቸውን የገለጹት ሌላኛው አስተያየት ሰጪ መምህር አጥናፉ አሰፋ፣ ለኢትዮጵያ የከፍታ ጉዞና ለህዝቦቿም የተስፋ መሰረት መሆኑን ተናግረዋል።
ሕብረት ካለ ፈተናን ተቋቁሞ ሌላም ታሪክ መስራት እንደሚቻል የሕዳሴው ግድብ ተጨባጭ ማሳያ ነው ያሉት መምህር አጥናፉ፣ የግድቡ መመረቅ ትልቅ ደስታ እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል።
የሕዳሴው ግድብ የኢትዮጵያ ማንሰራራት ጅማሮ ማብሰሪያና የአዲስ ዓመት ሰጦታችን ነው ያሉት ሌላው ነዋሪ ወይዘሮ ትዕግስት ደሳለኝ ናቸው።
ኢትዮጵያዊያን እንችላለን በሚል መንፈስና ወኔ ከተነሳን ሌላም ደማቅ ታሪከ መስራት አያቅተንም ያሉት ወይዘሮዋ፣ የዓመታት ልፋታችን ለፍሬ በቅቶ በማየቴ እድለኛ ነኝ ብለዋል።
"የሕዳሴ ግድብ ከሀይል ማመንጫነት ባሻገር በህዝቡ ላይ የይቻላል መንፈስን ከፍ ያደረጋና ኢትዮጵያ በራሷ እቅም ሜጋ ፕሮጀክቶችን ጀምራ ማጠናቀቅ እንደምትችል ለዓለም ያሳየችበት ዳግማዊ አድዋችን ነው" ሲሉም ወይዘሮ ትዕግስት ገልፀዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሁሉም ኢትዮጵያውያን አሻራ ያረፈበት፣ ብዙ ዋጋ የተከፈለበት እና የአብሮነታችን አርማ ነው ያሉት ደግሞ ሌላኛው የቦንጋ ከተማ ነዋሪ ምክትል ኮማንደር ወዳጆ ቡሾ ናቸው።
ለግድቡ ግንባታ ከደመወዛቸው በሦስት ዙር ቦንድ በመግዛት አስተዋጾ ማድረጋቸውን ጠቅሰው፣ ኢትዮጵያውያን ለፈተና ሳንበገር ግድቡን በራስ አቅም ገንብተን እውን በማድረጋችን የተለየ ደስታ እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል።
በቦንጋ ከተማ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መመረቅን አስመልክቶ የከተማ ነዋሪዎች ደስታቸውን በተለያየ መንገድ ገልጸዋል ።