ቀጥታ፡

የህዳሴ ግድብ የህብረ ብሄራዊ አንድነት ምልክትና የመቻል አቅማችን ማሳያ ነው

ወልቂጤ፤ ጳጉሜ 4/2017 (ኢዜአ):-  የህዳሴ ግድብ የህብረ ብሄራዊ አንድነት ምልክትና የመቻል አቅማችን ማሳያ ነው ሲሉ የወልቂጤ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ ። 

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቆ የተለያዩ አገራት መሪዎች በተገኙበት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)በይፋ ተመርቋል።

የግድቡን መመረቅ ተከትሎ ኢትዮጵያዊያን ከዳር ዳር በየአደባባዮቹ በመውጣት በተለያዩ መንገዶች ደስታቸውን ገልጸዋል።

በጉራጌ ዞን የወልቂጤ ከተማም ነዋሪዎች በተመሳሳይ ደስታቸውን የገለጹ ሲሆን የኢዜአ ሪፖርተር ስፍራው ላይ ተገኝቶ የተለያዩ ሰዎችን አነጋግሯል።

አስተያየታቸውን ከሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ወጣት ጃፋር ጀማል፣ መስቀሉ ምራጋ እና ሀሺም መሃመድ፤ በብዙ ውጣ ውረድ አልፈን ለዚህ ታላቅ ቀን በመብቃታችን ሁላችንም ተደስተናል ሲሉ ተናግረዋል። 

ሌላኛው የከተማው ነዋሪ አቶ ትግስቱ ፉጄ፤ የ14 ዓመታት የጽናት እና የልፋት ውጤት ተሳክቶ ከማየት በላይ ደስታ እንደሌለ አንስተው ሁላችንም እንኳን ደስ ያለን ብለዋል።

የጉራጌ ዞን መንገድ እና ትራንስፖርት መምሪያ ሃላፊ ትብለጥ ኢስጢፋኖስ፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከኢኮኖሚ ፋይዳውም ባለፈ በራሳችን አቅም ገንዘብና ጉልበት የገነባነው ዘመን የማይሽረው የታሪክ አሻራችን በመሆኑ ተደስተናል ብለዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም