ቀጥታ፡

የህዳሴ ግድብ ግንባታን ከፍጻሜ ለማድረስ ያደረግነው ድጋፍ ለውጤት በመብቃቱ ደስታ ተሰምቶናል

መቱ፤ ጭሮ፤ ጳጉሜ 4/2017 (ኢዜአ)፡- የህዳሴ ግድብ ግንባታን ከፍጻሜ ለማድረስ ያደረጉት ድጋፍ ለውጤት በመብቃቱ ታላቅ ደስታ እንደተሰማቸው በኦሮሚያ ክልል የመቱ እና የጭሮ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

የሕዳሴ ግድብን ከነበሩበት ውስብስብ ችግሮች በማውጣት ለዚህ ፍጻሜ ያበቁት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የለውጡ አመራሮች ትልቅ ምስጋና ይገባቸዋል ሲሉም ተናግረዋል።


 

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅና መመረቅን ተከትሎ የኢሉአባቦር ዞንና መቱ ከተማ ነዋሪዎች እንዲሁም የጭሮ ከተማ ነዋሪዎች በአደባባይ ደስታቸውን ገልጸዋል።

በሕዝቡ የደስታ መግለጫ ሰልፍ ላይ የተገኙት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ እንደገለጹት ግድቡ የኢትዮጵያን ከፍታ የሚያፋጥን ነው ብለዋል።

ዛሬ ብዙ ፈተናዎችን አሸንፈንና ተግዳሮቶችን ተሻግረን ከአንዱ ምዕራፍ ወደ ሌላኛው ምዕራፍ የተሸጋገርንበት ታሪካዊ ቀን ነው በማለትም ሌላ የአድዋ ታሪክ ደግመን ያስመዘገብንበት ቀን ነው በማለት ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን አሁን የጀመረችውን ከፍታ የማስቀጠል ትልቅ ኃላፊነት በመሆኑ አንድነታችንን ይበልጥ በማጠናከር በመንግስት የሚቀረጹ ልማቶችን በመተግበር የሀገራችንን እድገት ለማፋጠን እንሰራለን ያሉት ደግሞ አቶ አድነው ደምሴ ናቸው።

አቶ ያደታ ጂራኔ በበኩላቸው በራሳችን አቅም መልማትና ማደግ የምንችል መሆናችንን ለማረጋገጥ ከመንግስት ጎን ሆነን እንሰራለን ብለዋል።

በተመሳሳይ በምዕራብ ሀረርጌ ዞን ጭሮ ከተማ በተደረገ የድጋፍ መግለጫ ሰልፍ ላይ የተገኙት አቶ  ጠሀ አህመድ እንዳሉት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሁሉም ኢትዮጵያውያን አሻራ ያረፈበትና የዜጎችን አንድነትና መተሳሰር ያጠናከረ ፕሮጀክት ነው፡፡

''ከወርሀዊ ደመወዝ በማዋጣት አሻራዬን በማኖሬ ታላቅ ደስታ ይሰማኛል'' ያሉት አቶ ጠሀ በቀጣይ በሚካሄዱ ትላልቅ ልማት ፕሮጀክቶች ላይ በንቃት ለመሳተፍ ተነሳሽነት እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል፡፡

 ረዳት ኢንስፔክተር ሀብታሙ ኦላና፤ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለአገር ዕድገትና ብልጽግና ከሚኖረው ጠቀሜታ ባለፈ አገራችን በአካባቢያዊና አለም አቀፋዊ ጉዳዮች ይበልጥ ተጽዕኖ ፈጣሪ እንድትሆን ትልቅ አቅም የሚፈጥር ነው፡፡

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ  ግንባታ  መጠናቀቅ የኢትዮጵያ ክብር ከፍ የሚያደርግ እና ኢትዮጵያን በኩራት ከፍ ብለው እንዲሄዱ የሚያደርግ ታላቅ ድል ነው ያሉት ደግሞ የከተማው ነዋሪ አቶ ከድር ሰይድ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም