የህዳሴ ግድብ መመረቅ ባለፉት ዘመናት የዘመናት የትውልድ ቁጭትን የመለሰ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የህዳሴ ግድብ መመረቅ ባለፉት ዘመናት የዘመናት የትውልድ ቁጭትን የመለሰ ነው
ወላይታ ሶዶ፣ ጳጉሜ 4/2017(ኢዜአ):- የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መመረቅ የዘመናት የትውልድ ቁጭትን የመለሰ ታላቅ ተግባር መሆኑ ተገለፀ።
የህዳሴ ግድብ ምረቃን አስመልክቶ ደማቅ የደስታ መግለጫ ህዝባዊ ሰልፍ በወላይታ ሶዶ ከተማ ተካሄዷል።
በሰልፉ ላይ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ እና የወላይታ ሶዶ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ተፈሪ አባተ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መመረቅ የዘመናት የትውልድ ቁጭትን የመለሰ ታላቅ ተግባር ነው ብለዋል።
የግድቡ መጠናቀቅ ኢትዮጵያውያን በተባበረ ክንድ ድህነትን ለማሸነፍ ያደረጉት ትግል በቆራጥ መሪ ወደ ውጤት የተቀየረበት መሆኑን አንስተው ህዝብና መንግስት በተሰናሰለ ክንድ ያመጡት የሀገራችን ማንሰራራት ማሳያ መሆኑን ገልፀዋል።
የህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ለኢትዮጵያ ትንሳኤ የመፍትሄና የብልጽግና ግብ መሰረት እንደሚሆንም ተናግረዋል።
የአይቻልም መንፈስ በአንድነት ተቀልብሶ በህዳሴ ግድብ ታሪክ ተሰርቷል ያሉት ደግሞ የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ረዳት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ተሰማ ናቸው።
የህዳሴ ግድብ ስኬት ለኢትዮጵያውያን ዘርፈ ብዙ ትርጉምን እንደሚሰጥ ጠቁመው ይህም የመቻልን ወኔ ያላበሰ አሻራ ያረፈበት እንደሆነም ተናግረዋል።
በብዙ ውጣ ውረዶች ያለፈው የግድቡ ግንባታ የዘመናት የትውልዱን የመልማት ቁጭት ለማሳካት በተወሰደው ቁርጠኛና በሳል አመራር ለዛሬ ምረቃ በመብቃቱ ደስታችን ድርብ ነው ብለዋል።
በአፍሪካ ቀዳሚ የሆነ ግዙፍ ግድብን በተባበረ ክንድ ያሳካነው የማደግ ህልማችንን እና ራዕይ በተግባር ለማሳየት የተደረገ ትግል ውጤት መሆኑን ጠቅሰው ይህ የመደመርና የመልማት አቅም በሌሎች የልማት መስኮችም መድገም እንደምንችል ያሳያል ብለዋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪ አቶ ተሐሴ ቴቃ በበኩላቸው በርካታ ፈተናዎችን ያለፈው የህዳሴ ግድብ በመመረቁ የተሰማቸው ደስታ ወደር እንደሌለው ገልጸዋል።
ወይዘሪት ወይንሸት መና የተባሉ ሌኛዋ አስተያየት ሰጪ እንዳሉት፤ የግድቡ መጠናቀቅ የመሪዎችን ቁርጠኝነት ከማሳየቱም በላይ የህዝቡንም ችግር በዘላቂነት የሚፈታ በመሆኑ በቀጣይ ሌላ ሀገራዊ ፕሮጀክት ለመስራት አነሳስቶናል ብለዋል።
የተለያዩ የህዝበረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት የደስታ መግለጫ ስነ-ስርዓቱም በእግር ጉዞ፣ በተሽከርካሪ ትዕይንትና የግድቡ ግንባታ ሂደትን በሚያወሱ መፈክሮች የታጀበ ነበር።