ኢትዮጵያ ዛሬ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍ ያለችበት እለት ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ዛሬ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍ ያለችበት እለት ነው
ሆሳዕና፤ ጳጉሜን 4/2017 (ኢዜአ) :- ኢትዮጵያ ዛሬ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍ ያለችበት እለት ነው ሲሉ የሆሳእና ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።
የሆሳእና ከተማ ነዋሪዎች የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ምረቃን አስመልክተው ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት የዘመናት የመልማት ቁጭታችን ማሳኪያ የሆነው የሕዳሴው ግድብ ኢትዮጵያ የልማት ትልሟን ማሳካት እንደምትችል አንዱ ማሳያ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
በሆሳዕና ከተማ ሄጦ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ዘለቀ ማርቆስ እንዳሉት የትብብራችን ውጤት የሆነው የሕዳሴ ግድብ ግንባታ በመጠናቀቁ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቷቸዋል።
ግድቡ ኢትዮጵያ የልማት ትልሟን ማሳካት እንደምትችል አንዱ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።
ግድቡ ለምረቃ መብቃቱ በቀጣይ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ገንብቶ ለማጠናቀቅ መነሳሳት የሚፈጥር መሆኑን ጠቅሰው ፤ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍ ያለችበት እለት ነው ብለዋል።
ግድቡ የመላው ኢትዮጵያውያን የትብብር ውጤት ነው ያሉት ደግሞ በከተማዋ የሴች ዱና ቀበሌ ነዋሪ አቶ ደጀኔ አወቀ ናቸው፡፡
ግድቡ ለዘመናት በኢትዮጵያውያን ዘንድ የነበረን ቁጭት ያስቀረ ስለመሆኑም ጠቁመዋል፡፡
ትራፊክ ፖሊስ ኢንስፔክተር በላይነሽ ዘለቀ በበኩላቸው የሕዳሴ ግድብ ተጠናቆ ለምረቃ በመብቃቱ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፤ የጀግኖች አባቶቻችንን የአድዋ ታሪክ የደገምንበትና የተጋራንበት ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነን ተባብረን ከሰራን የተሻለች ሀገር መፍጠር እንደምንችል ማሳያ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
የግድቡ ምረቃት የተለየ ስሜት እንደፈጠረባትና “በሕዳሴው ግድብ የታየውን ትብብር በሌሎች ሀገራዊ ፕሮጀክቶች መድገም ይጠበቅብናል ያለችው ደግሞ በከተማው የአራዳ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት እፁብ ከፈለኝ ናት፡፡