ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን አንድነትና ፅናት የታየበት አኩሪ ፕሮጀክታችን ነው-የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን አንድነትና ፅናት የታየበት አኩሪ ፕሮጀክታችን ነው-የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች
ባሕር ዳር፤ጳጉሜን 4/2017(ኢዜአ)፡-ታላቁ የሕዳሴው ግድብ በስኬት መጠናቀቅ የኢትዮጵያውያን አንድነት፣ፅናትና ትብብር የታየበት አኩሪ ፕሮጀክታችን ነው ሲሉ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።
ነዋሪዎቹ ግድቡ ተጠናቆ ለምረቃ በመብቃቱ የተሰማቸውን ደስታ በከተማው በጋራ በመሰብሰብና በተሽከርካሪዎች በመንቀሳቀስ ጭምር ገልጸዋል።
ከነዋሪዎቹ መካከል ወንድም ዋለልኝ ለኢዜአ እንዳሉት፥ የሕዳሴ ግድቡ መጠናቀቅ ዛሬ ለመላው ኢትዮጵያውያን አዲስ የተስፋ ብርሃን የፈነጠቀበት ልዩ ቀን ነው።
የግድቡን ፍፃሜ በጉጉት እንጠብቀው ነበር ያሉት ነዋሪው፥በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፎ የመጠናቀቁን ዜና በሰሙበት ወቅት ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ተናግረዋል።
ለግድቡ ግንባታ መሳካት በልጃቸውም ሆነ በራሳቸው ስም ቦንድ በመግዛት አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን አስታውሰው፥ፍሬውን ማየት በመቻላቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።
የግድቡ ግንባታ ከዚሕ ደረጃ እንዲደርስ የመላ ኢትዮጵያውያን አንድነት፣ትብብር፣ሕብረትና ፅናት የታየበት አኩሪ ፕሮጀክታችን ነው ብለዋል።
ታላቁ የሕዳሴ ግድብ መስዋዕትነት ጭምር ተከፍሎበት ለውጤት የበቃና የመሪዎች ቆራጥነት የተረጋገጠበት ስኬት መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ወይዘሮ አታሌ ነጮ ናቸው።
ለግድቡ ግንባታ የመሰረት ድንጋዩ ከተቀመጠበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን የገንዘብ መዋጮ እንዳደረጉና በመጠናቀቁ ኩራት እንደተሰማቸው ገልጸዋል።
በግድቡ ግንባታ ሂደት የኢትዮጵያውያን አይበገሬነት ለመላው ዓለም በተግባር ያሳዩበትና የዲፕሎማሲ የበላይነት የተንፀባረቀበት ነው ብለዋል።
ሌላው የከተማው ነዋሪ ዳዊት ሞት ባይኖር በበኩላቸው፥ታላቁ የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ የአይቻልምን መንፈስ የሰበረና የይቻላንን ጉልበት የጨመረ ፕሮጀክት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በዚሕም የኢትዮጵያ ሕዝብ ትብብርና አንድነት እንዲሁም ለሃገር ፍቅርና ልማት ያላቸውን ቁርጠኝነት በተግባር የታየበት እንደሆነ አብራርተዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው፥ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ከፍታና የስልጣኔ ቀደምትነትን የደገመ ነው ብለዋል።
ለግድቡ ግንባታ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ያሳያው ያልተቋረጠ ድጋፍና ትብብር ለሃገሩ ያለውን ፍቅር፤ ፅናትና አይበገሬነት ያረጋገጠበት እንደሆነም አብራርተዋል።