ዛሬ ለመላው ኢትዮጵያውያን ታላቅ ድል ነው - አሽከርካሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ዛሬ ለመላው ኢትዮጵያውያን ታላቅ ድል ነው - አሽከርካሪዎች
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 4/2017(ኢዜአ)፦ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተጠናቆ ለምረቃ መብቃቱ ለመላው ኢትዮጵያውያን ታላቅ ድል ነው ሲሉ በአዲስ አበባ የተሽከርካሪዎች የጎዳና ላይ ትርኢት የተሳተፉ አሽከርካሪዎች ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያውያን ሕብረ ብሔራዊነት መገለጫ የሆነውን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ዛሬ ጳጉሜን 4 ቀን 2017 በይፋ መርቀዋል፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ምረቃን አስመልክቶ በአዲስ አበባ የተሽከርካሪዎች የጎዳና ላይ ትርኢት ተካሂዷል።
በትርኢቱ ካነጋገርናቸው አሽከርካሪዎች መካከል ስለሺ ወግደረሰኝ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን በጋራ ያሳኩት ድል መሆኑን ገልጸዋል።
ታላቁ የህዳሴ ግድብ የሁሉም ኢትዮጵያውያን የልፋት ውጤት መሆኑን ገልጸው፤ ግንባታው ተጠናቆ ምረቃውን ማየት ደስታን የሚፈጥር መሆኑን ጠቅሰዋል።
ሌላኛዋ አስተያየት ሰጭ ቅድስት ሸዋንግዛው በበኩሏ፤ የታላቁ ህዳሴ ግድብ መመረቅ ለመላው ኢትዮጵያውያን ደስታን የሚፈጥር መሆኑን ተናግራለች።
ታላቁ ህዳሴ ግድብ እድገት እና ልማትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጻለች።
ሌላኛው አስተያየት ሰጭ ተሾመ መኮንንም የታላቁ ህዳሴ ግድብ በኢትዮጵያ ትልቅ ታሪክ ተደርጎ የሚወሰድ መሆኑን ገልጸዋል።
ታላቁ የህዳሴ ግድብ እውን መሆኑ በቀጣይም ብዙ ፕሮጀክቶችን በራስ አቅም ለማከናወን በተግባር ያሳየ መሆኑን ጠቅሰው፤ ግድቡ የአገር ሀብት በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊጠብቀው እንደሚገባ ተናግረዋል።
ብስራቱ ለኢትዮጵያውን ታላቅ ድል መሆኑን የገለጸችው ምህረት ጥላሁን፤ በታላቁ ህዳሴ ግድብ የታየው መተባበር እና አንድነትም በሌሎች ስራዎች ላይ መደገም እንዳለበት አስተያየቷን ሰጥታለች።
የግድቡን ፍጻሜ በዚህ ዘመን ማየታችን እድለኛ ያደርገናል ያለው ተስፋዬ ገብረሚካኤል በበኩሉ፤ ታላቁ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን ታላቅ ፕሮጀክት ነው ብሏል።