ቀጥታ፡

የነገው ቀን የኢትዮጵያን መሻት እውን ለማድረግ አገራዊ ዝግጁነትን በሚያሳይ መልኩ ይከበራል - የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 4/2017(ኢዜአ)፦ የነገው ቀን የኢትዮጵያን መሻት እውን ለማድረግ አገራዊ ዝግጁነትን በሚያሳይ መልኩ የሚከበር መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ኢትዮጵያ የጳጉሜን ቀናት አገራዊ አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ በተለያዩ ስያሜዎች እያከበረች ትገኛለች።

በዚህ መሰረት ጳጉሜን 1 የጽናት፣ ጳጉሜን 2 የህብር፣ ጳጉሜን 3 የእመርታ፣ ጳጉሜን 4 የማንሰራራት በሚል በተለያዩ ኹነቶች የተከበሩ ሲሆን፤ ነገ የመጨረሻዋ ጳጉሜን 5 ደግሞ የነገ ቀን የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል።

''ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ማድረግ'' በሚል መሪ ሀሳብ የሚከበረው የነገ ቀን ኢትዮጵያ በዲጂታል ቴክኖሎጂ እያከናወነቻቸው ያሉ ሥራዎች ላይ ትኩረት ባደረጉ ሁነቶች ላይ ያተኩራል ተብሏል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ በለጠ ሞላ (ዶ/ር)የነገን ቀን አስመልክቶ ለኢዜአ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በዚሁ ወቅት ኢትዮጵያ በዘመናት ውጣ ውረድ ውስጥ በርካታ ሂደቶችን አልፋለች ብለዋል።

ዛሬ የትናንት ድምር ውጤት መሆኑን ጠቅሰው፤ ነገን የተሻለ የማድረግና መሻታችንንና ዝግጁነታችንን በነገ ቀን እናሳያለን ብለዋል።

የነገው ቀን ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ ራሷን መቻል የሚያስችሏት መሰረቶች እየተጣሉ መሆኑን የገለጹት ሚኒሰትሩ፤ የምግብ ሉዓላዊነት ማረጋገጥና የአደጋ ስጋት ምላሽን በራስ አቅም የመከወን መሻቶችን እውን ለማድረግ አገራዊና ዜጋዊ ዝግጁነት በሚያሳይ መልኩ ይከበራል ብለዋል።

በሳይንስ ሙዚየም በተለያዩ ኹነቶች ቀኑ እንደሚከበር የገለጹት ሚኒስትሩ፤ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚሳተፉባቸው የፓናል ውይይቶች ይካሄዳሉ ብለዋል።

ኢትዮጵያ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ከአምስት ዓመት በፊት ጅማሮ ላይ እንደነበረች የገለጹት ሚኒስትሩ፤ የአምስት ዓመት የዲጂታል ስትራቴጂ ተቀርጾ ወደ ሥራ መገባቱ ተጨባጭ ለውጦች እንዲመጡ አድርጓል ብለዋል።

ይሁንና አገሪቷ ካሏት እምቅ አቅም አኳያ የዲጂታል ኢትዮጵያን ነገ የተሻለ ለማድረግ ቀሪ ሥራዎች አሉ ብለዋል።

የነገዋን ኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታው እውን እንዲሆን በጥንካሬ ይሰራል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም