ቀጥታ፡

የህዳሴ ግድብ የአባቶቻችን ምኞት እውን የሆነበት ፕሮጀክት ነው

ጋምቤላ፤ ጳጉሜ 4/2017(ኢዜአ)፡-ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የአያቶቻችንና አባቶቻችን ምኞት እውን የሆነበት ፕሮጀክት ነው ሲሉ የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቆ ለምረቃ መብቃቱን ተከትሎ ደስታቸውን በተለያዩ ሁነቶች ገልጸዋል።

በከተማው ደስታቸውን ሲገልጹ ካገኘናቸው ነዋሪዎች መካከል አቶ ፓራኖክ ዋዋይ በሰጡት አስተያየት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ  ለምረቃ መብቃቱ  የኢትዮጵያን ከፍታ ማሳያ  ነው  ብለዋል።

ይህም  የሀገሪቱን የማንሰራራት  ግብ እውን  ለማድረግም አበርክቶው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

የግድቡ   መመረቅ ኢትዮጵያውያን በመተባበር  ታላላቅ ፕሮጀክቶችን ማሳካት እንደሚችሉ ያሳየ መሆኑን የገለጹት ደግሞ ሌላው  አስተያየት ሰጪ አቶ አስምሮ ደርበው ናቸው።

ቀደምት አባቶቻችን በአንድነት ሆነው በአድዋ ጦርነት ያስመዘገቡትን ታሪካዊ ድል የአሁኑ ትውልድ ደግሞ ታላቁ የኢትዮጰያ ህዳሴ ግድብን ገንብቶ በማጠናቀቅ ደግሞታል ብለዋል።

ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ ኡቦንግ ኡጉታ በሰጡት አስተያየት አባቶቻችን በዓባይ ወንዝ የመጠቀም የዘመናት ህልም በዚህ ትውልድ እውን በመሆኑ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ተናግረዋል።

ግድቡ የሁሉም የኢትዮጵያ ዜጋ አሻራ ያረፈበትና አንድነታቸውን ያሳዩባት ታሪካዊ ፕሮጀክት በመሆኑ ልንኮራ ይገባልም ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን ከተባበሩና በአንድነት ከቆሙ የማይሻገሩት ፈተናና የማያሳኩት ህልም አይኖርም ስትል የተናገረቸው ደግሞ ወጣት ሀና ገዛኸኝ ናት።

ስለሆነም በህዳሴው ግድብ ግንባታ የታየው አንድነትና ትብብር በሌሎችም የልማት ስራዎች በመድገም የኢትዮጵያን ከፍታ ልናረጋግጥ ይገባል ስትል ወጣቷ ተናግራለች።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም