ቀጥታ፡

የሕዳሴ ግድቡ የታሪካችን እጥፋትና ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ የሚወስድ ፕሮጀክት ነው-የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት

አዲስ አበባ፤ጳጉሜን 4/2017 (ኢዜአ)፡-ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የታሪካችን እጥፋትና ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ የሚወስድ ፕሮጀክት መሆኑን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታወቀ።

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በመጠናቀቁ የተሰማውን ደስታ ገልጿል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለኢዜአ በላከው መግለጫ ፥ ''ኢትዮጵያውያን በተከታታይ ትውልዶች ሲዘከር የሚኖር ትልቅ አሻራ በማኖራችሁ እንኳን ደስ አላችሁ'' ብሏል።

የሕዳሴ ግድቡ የታሪካችን እጥፋትና ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ የሚወስድ ፕሮጀክት መሆኑን አመልክቷል፡፡

ከመቆጨትና ከቁዘማ በመውጣት በአፍሪካ አንደኛ የሆነ ግድብ በራሳችን አቅም መሥራት መቻል ትልቅ የሥነ-ልቦና ከፍታን እንደሚያስገኝ፤ በተጨባጭ የሚታይ የእይታና የከፍታ ለውጥ እንደሚያመጣም አስታውቋል፡፡

ሀገራችን በአባይ ወንዝ ላይ ግድብ እንዳትሰራና እንዳታለማ ድጋፍና ብድር እንዳታገኝ ሲደረግ ነበር፡፡ በራሳችን ገንዘብና በሕዝብ ጉልበት ግድቡን መሥራት መቻል ትልቅ ድል ነው ብሏል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ቁልፍ መሰረት ልማቶችን በመጠበቅ ረገድ በአዋጅ በተሰጠው ስልጣን በግድቡ ግንባታ ሂደት በመረጃ ልቆ በመገኘት፣ አስቀድሞ አደጋን በማነፍነፍ እና ለመከላከል የሚያስችሉ ሥራዎችን በቴክኖሎጂ ታግዞ በማከናወን፤ ከግድቡ ጋር በተያያዘ የተከፈተውን የሥነ-ልቦና ጦርነትና ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎች በመመከት እንዲሁም መላው ሰራተኛም በቦንድ ግዢ ከፍተኛ ሚና አበርክቷል ያለው መረጃው፤ የተቋሙ አባላት እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ድረስ በመክፈል ግድቡ ለፍጻሜ እንዲበቃ በማድረጋቸው ምስጋና እንደሚገባቸው አስታውቋል፡፡

መላው የኢትዮጵያ ሕዝብም በተለያየ ደረጃ የሚገለጽ አስተዋጽዖ በማበርከት ግድቡ እንዲጠናቀቅ ያደረገው ርብብር በታሪክ ሲወሳ የሚኖር ነው ብሏል፡፡

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ( ዶ/ር) ግድቡ ከፍጻሜ እንዲደርስ በሳልና ቁርጠኛ አመራር በመስጠት ያበረከቱት ሚና ለሀገራችን የማንሠራራት ጉዞ አዲስ ምዕራፍ መሆኑን አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ለኢዜአ የላከው መረጃ አመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም