ለህዳሴ ግድብ ያደረግነው ድጋፍ በሌሎች ፕሮጀክቶች ላይ እንደግመዋለን - የድሬዳዋ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ለህዳሴ ግድብ ያደረግነው ድጋፍ በሌሎች ፕሮጀክቶች ላይ እንደግመዋለን - የድሬዳዋ ነዋሪዎች
ድሬደዋ፣ ጳጉሜ 4/2017(ኢዜአ):- ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ያደረግነውን ድጋፍ በሌሎች ፕሮጀክቶች ላይም እንደግመዋለን ሲሉ የድሬዳዋ አስተዳደር ነዋሪዎች ገለጹ።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ምረቃን አስመልክቶ የድሬዳዋ አስተዳደር ነዋሪዎች ደስታቸውን በአደባባይ ገልጸዋል።
በዚሁ ወቅት አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ የአስተዳደሩ ነዋሪዎች መካከል የድሬደዋ የሶማሌ የቲያትር ቡድን አስተባባሪ ወይዘሮ ኮውሰር መሐመድ እንዳሉት፤ የህዳሴ ግድብ ተጠናቆ መመረቅ የሀገራችንን የማንሰራራት ዘመን ማሳያ ነው።
ዛሬ በማንሰራራት ቀን ይህን ታላቅ ብስራት መስማታችን ደስታችን ወሰን የለውም ያሉት ወይዘሮ ኮውሰር፤ ለግድቡ ግንባታ ህዝብን በማስተባበርና ቦንድ በመግዛት ያሳዩትን ተሳትፎ በሌሎችም ፕሮጀክቶች ላይ ለመድገም አነሳስቷቸዋል።
የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት አባል አቶ አበጀ ንጋቱ በበኩላቸው የህዳሴ ግድብ የሀገራችን ብልፅግና ጉዞ በትክክል እንደሚሳካ ያረጋገጠ የኢትዮጵያ ግዙፍ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።
በአዲሱ ዓመትም ተመሳሳይ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት በአንድነት መነሳት አለብን ብለዋል።
ዛሬ በድሬዳዋ ጎዳናዎች ደስታቸውን ከገለጹት መካከል የታክሲ አሽከርካሪዎች ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ናቸው።
ከእነዚህ አሽከርካሪዎች መካከል አቶ ሙክታር ሁሴን እንዳሉት ታላቁ የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን ህብረትና አንድነት መገለጫ እና የልጆቻችን ቀጣይ ተስፋ ያበበበት ታላቅ ፕሮጀክት ነው።
"ለግድቡ በማህበር ተደራጅተን ያደረግነውን ድጋፍ በአዲሱ ዓመት ሌሎች ፕሮጀክቶችን ጀምረን ለማሳካት እንረባረባለን" ብለዋል።
ለግድቡ ዕውን መሆን እኛም የድርሻችንን ተወጥተናል ያሉት አቶ ናስር መሐመድ ፕሮጀክቱ ለእኔና ለቤተሰቤ የአዲስ ዓመት ስጦታ በመሆኑ ተደስቻለሁ ብለዋል።