ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለምረቃ በመብቃቱ ደስታና ኩራት ተሰምቶናል--የአርባ ምንጭ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለምረቃ በመብቃቱ ደስታና ኩራት ተሰምቶናል--የአርባ ምንጭ ነዋሪዎች
አርባ ምንጭ ፤ጳጉሜን 4/2017 (ኢዜአ):- በጉጉት ስንጠብቀው የነበረውና የጽናት ማሳያ የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተጠናቅቆ ዛሬ ለምረቃ በመብቃቱ ደስታና ኩራት ተሰምቶናል ሲሉ የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች እንደገለፁት፤ ግድቡ ለኢትዮጵያ ህዝብ ቅንጦት ሳይሆን ከጨለማ የምንላቀቅበት ነው።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ ኤልያስ ኤና፤ በራሳችን ገንዘብ፣ ጉልበትና ላብ በመተባበር የገነባነው ግድብ መጠናቀቁ የጀመርነውን መጨረስ እንደምንችል ለዓለም ይመሰክርልናል ብለዋል።
ግድቡ ብዙ የውስጥና የውጭ ፈተናዎችን ተቋቁሞ ለምረቃ በመብቃቱም መደሰታቸውን ገልጸዋል።
ሌላኛዋ የከተማው ነዋሪ ሲስተር ውድነሽ ዶሳ በበኩላቸው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በገጠሩ የሃገራችን ክፍል የሚኖሩ አያሌ ሴቶችን በጭስ ከመታፈን በመታደግ የሴቶችን ችግር በመሠረታዊነት የሚፈታ ነው ብለዋል።
ግድቡ ሁለንተናዊ ብልጽግናን በማረጋገጥ ባሻገር የኑሮ ዘይቤያችንን የሚቀይር ብሎም ከጎረቤት ሀገራት ጋር ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋገጥ ነው ያሉት።
አያቶቻችን በመተባበር የአድዋን ድል እንዳስመዘገቡ ሁሉ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለምረቃ መብቃቱን በማየታችን ደስታና ኩራት ተሰምቶኛል ብለዋል ሲስተር ውድነሽ።
ግድቡ የሁሉም ኢትዮጵያውያን አሻራ ያረፈበት ከዳር እስከ ዳር ህዝቡን ያስተሳሰረ ታሪካዊ ፕሮጀክት ነው ያለው ደግሞ ወጣት ታረቀኝ ገረሡ ነው።
ለወጣቱ በርካታ የሥራ በሮችን የሚከፍት የህልውና ፕሮጀክት መሆኑን ጠቅሶ እንደ አይናችን ብሌን እንጠብቀዋለን ብሏል።
በቀጣይም እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ያሉ ሌሎች ፕሮጀክቶችን ለመፈጸምም ወጣቱ ጠንክሮ መስራት እንደሚገባውም አመልክቷል።