ቀጥታ፡

የሕዳሴው ግድብ ትውልዱ ታሪክን ከመናገር ባለፈ የራሱን ደማቅ ታሪክ መጻፍ እንደሚችል ያረጋገጠበት ነው

ሚዛን አማን፣ ጳጉሜን 4/2017 (ኢዜአ)፡-ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ትውልዱ ታሪክን ከመናገር ባለፈ የራሱን ደማቅ ታሪክ መጻፍ እንደሚችል በተግባር ያረጋገጠበት መሆኑ ተገለጸ።

ዘላቂ ልማት ለሀገራዊ ማንሠራራት በሚል መሪ ቃል ጳጉሜን 4 -የማንሰራራት ቀን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ሚዛን አማን ከተማ ተከብሯል።


 

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ መሠረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ፋጂዮ ሳፒ በወቅቱ እንዳሉት ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፍ እያንሰራራች ነው።

የማንሠራራት ጅማሮ የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሁላችንም አሻራ ያረፈበት የአንድነታችን መሰሶ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

በጠንካራ መሪዎቻችንና በመላው ኢትዮጵያዊያን ዋጋ የተከፈለበት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኃይል ከማመንጨት ባሻገር የ"ይቻላል" ትርክትን ለዓለም ያሳየንበት ፕሮጀክታችን ነው ብለዋል። 

የዛሬው ትውልድ ታሪክ  ከመናገር ባለፈ የራሳችንን  ደማቅ ታሪክ መሥራት የጀመርንበት የማንሠራራት ጅማሮ በመሆኑ  የልማት ተግባሩን  ማጠናከር ይጠበቅብናል ሲሉም አክለዋል።


 

የቤንች ሸኮ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍትን በበኩላቸው ሕብረታችንን በማጠናከር ሜጋ ፕሮጀክቶችን ጀምረን መጨረስ እንደምንችል ደማቅ ታሪክ የጻፍንበት ነው ሲሉ ገልጸዋል።

በህዝብ የነቃ ተሳትፎ እየተመዘገቡ ያሉት የልማት ውጤቶች የአሁኑ ትውልድ ያስመዘገበው ዳግማዊ ዓድዋ መሆኑንም አንስተዋል።

የማንሠራራት ቀን የፓናል ውይይት ላይ ከተሳተፉት መካከል አቶ ሽመልስ መኩሪያ እንደሀገር እየተመዘገቡ ያሉ የልማት ውጤቶች ኢትዮጵያን ወደ ፊት የሚያራምዱ መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

በቀጣይ በአንድነት ቆመን ተጨማሪ ሜጋ የልማት ፕሮጀክቶችን ከስኬት ለማብቃት መነሳሳትን የፈጠረ ነው ብለዋል።

"ኢትዮጵያ ማንሰራራት ስለመጀመሯ አንዱ ማረጋገጫ ዛሬ ለምረቃ የበቃው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ነው ያሉት ደግሞ አቶ ካጁ አቤል የተባሉ የመድረኩ ተሳታፊ ናቸው።

ግድቡ የአሁኑ ትውልድ ደማቅ ታሪክ የተጻፈበት ቅርስ ነው ያሉት አቶ ካጁ፣ ታሪክ ከመንገር ባለፈ የራስን ደማቅ አሻራ ለማኖር የጀመርነውን ጉዞ ለማጠናከር አብሮነትን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

ከሕዳሴው ግድብ በመማር እንደሀገር የሚከናወኑ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን ለማፋጠን ለዘላቂ ሰላምና አብሮነት ትኩረት መስጠት እንደሚገባም ተናግረዋል።

ዛሬ የሚከበረውን የማንሠራራት ቀን ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀው የፓናል ውይይት ላይ የክልልና የዞን የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የተለያዩ ተቋማት ሠራተኞች ተገኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም