ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን ህልም እውን የሆነበት ነው - የጣሊያኑ ዊ ቢውልድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ ፔይትሮ ሳሊኒ - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን ህልም እውን የሆነበት ነው - የጣሊያኑ ዊ ቢውልድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ ፔይትሮ ሳሊኒ
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 4/2017(ኢዜአ)፦ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን ህልም የሆነበት ፕሮጀክት ነው ሲሉ የጣሊያኑ ዊ ቢውልድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ ፔይትሮ ሳሊኒ ገለጹ።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በዛሬው ዕለት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ተመርቋል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት ዋና ስራ አስፈጻሚው የጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ገልጸዋል።
የሕዳሴ ግድብ ግንባታ አሁን ላይ ተጠናቆ ሲታይ ለእይታ ቀላል ቢመስልም በርካታ ፈተናዎችን የተሻገረ ፕሮጀክት መሆኑን ተናግረዋል።
ግድቡ አሁን ላይ የሚያስፈልገውን ውሃ መያዙንና የሚያመነጨው ኢነርጂ በመላው ኢትዮጵያ እንደሚሰራጭ ጠቁመዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኔ ህልም እና የኢትዮጵያ ህልም እውን የሆነበት ነውም ብለዋል።
ከሕዳሴው ግድብ ከ35 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ኃይል እንደሚያገኝና የኢትዮጵያን የኢነርጂ አቅም በሶስት እጥፍ እንደሚጨምርም አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ለጎረቤቶቿ በመሸጥ ትብብሯን ማጠናከር እንደሚያስችላትና ይህም ቀጣናዊ ሰላምን ለማስፈን ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል።
የህዳሴ ግድብ በዓለማችን ደህንነታቸው ከተጠበቁ ፕሮጀክቶች አንዱ ነው ያሉት ሃላፊው ዜጎች በታላቅ ቁርጠኝነት እና መስተዋዕትነት ያሳኩት ፕሮጀክት ነው ብለዋል።
የግድቡ ግንባታ ጠንካራ የስራ ባህል እና ጽናት የታየበት መሆኑንም ነው የገለጹት።
ፕሮጀክቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የእውቀት፣ የቴክኖሎጂ እና የአቅም ሽግግር ያገኙበት እንደሆነም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያውያን በፈተናዎችና በችግሮች ውስጥ ሆነው ሳይበገሩ ግድቡ እንዲጠናቀቅ ትልቅ ሚና መጫወታቸውን አመልክተዋል።
በህዳሴ ግድብ የተሳተፉ ሰራተኞች፣ ቴክኒሺያኖች፣ መሐንዲሶች እና በግንባታው ላይ አሻራቸውን ያሳረፉ በሙሉ ምስጋና እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
ህዳሴ ግድብ ለቀጣይ ትውልዶች ብርሃንና ተስፋ የሆነ ፕሮጀክት ነው ሲሉም ገልጸዋል።