ቀጥታ፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ቀጣናውን በማስተሳሰር ረገድ የራሱን ሚና ያበረክታል - ሙሐሙድ አሊ ዩሱፍ

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 4/2017(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ በትውልድ ቅብብሎሽ ገንብታ ዛሬ ለምረቃ ያበቃችው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከሀገሬው አልፎ ለጎረቤት ሀገራት ብርሃን መሆኑን የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሐሙድ አሊ ዩሱፍ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዛሬው ዕለት ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መርቀዋል።

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ንግግር ያደረጉት የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሐሙድ አሊ ዩሱፍ እንዳሉት፤ ግድቡ በትውልድ ቅብብሎሽ ተገንብቶ ዛሬ ለምረቃ በመብቃቱ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና ለመላው ኢትዮጵያውያን እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጉዳይ በበርካታ ውስብስብና አድካሚ ሂደት አልፎ ዛሬ በስኬት በመቋጨቱ፤ በኢትዮጵያ ትልቅ ታሪክ መሠራቱን ይመሰክራል ነው ያሉት።


 

የፕሮጀክቱን የግንባታ ሂደት ፈታኝነት ጠቅሰው፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በሳል እና ጥበብ የተሞላበት አመራር ሰጭነት ለምረቃ መብቃቱን አንስተዋል።

የዚህ ፕሮጀክት ስኬት ከአኅጉራዊ አጀንዳዎች ጋር የሚጣጣም መሆኑን በመጥቀስ፤ ለአየር ንብረት የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ በመገንባት ኢትዮጵያንና ቀጣናውን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በራስ አቅም የገነባችው መሆኑንና ይህም ለአኅጉራችን መነሳሳትን የሚፈጥር ተግባር ነው ብለዋል።

በመሠረተ ልማት ተደራሽነት መርሐግብር መሠረት በኢነርጂ፣ በትራንስፖርት፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እና በሌሎችም አጀንዳ 2063ን ለማሳካት እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።

ትናንት በስኬት በአዲስ አበባ ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ መካሄዱን በማውሳት፤ ይህም ከታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዓላማ ጋር የሚሰናሰል መሆኑን አንስተዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ በአኅጉሪቱ የኢነርጂ ሽግግር እየተደረገ ለመሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል።

የግድቡ መገንባት በተፋሰሱ ሀገራት ላይ ጉዳት እንደማያስከትል በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተደጋጋሚ ሲገለጽ መኖሩንም አንስተዋል።

ውኃን በጋራ በሰላማዊ ሁኔታ ከመጠቀም አኳያና የራስን ችግር በራስ በመፍታት ረገድ በአኅጉራችን በአርዓያነት የሚጠቀስ ተግባር አለ ያሉት ሊቀመንበሩ፤ ከሴኔጋል ወንዝ ጋር በተያያዘ በሴኔጋል፣ ማሊ እና ሞሪታኒያ መካከል የተደረገውን የሦስትዮሽ ትብብር ለአብነት አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም