ቀጥታ፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ብሔራዊ ፕሮጀክት ብቻ ሳይሆን የፓን አፍሪካ ግልጽ አቋም ነው -ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ

አዲስ አበባ፤ጳጉሜን 4/2017(ኢዜአ)፦ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ብሔራዊ ፕሮጀክት ብቻ ሳይሆን የፓን አፍሪካ ግልጽ አቋም ነው ሲሉ የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ገለጹ፡፡

የኬንያ ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ምረቃ በዓል ላይ የተገኝተው ለኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት የእንኳን  ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የታላቁ ህዳሴ ግድቡ መሳካት የኢትዮጵያና የአፍሪካ ታላቅ ድል መሆኑንም ተናግረዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የምህንድስና ምኞት ብቻ ሳይሆን አፍሪካ የራሷን ዕጣ ፈንታ የመቅረፅ ብቃት እንዳላት የሚያሳይ ነው ብለዋል።

ሀብቷን የማስተዳደር እና ብልፅግናዋን የሚያሳኩ ወሳኝ መሠረተ ልማቶችን የማቅረብ አቅም እንዳላት በተጨባጭ ያስመሰከረ መሆኑንም ገልጸዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ብሔራዊ ፕሮጀክት ብቻ አይደለም ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ የአፍሪካን ዕጣ ፈንታ በራስ አቅም የመወሰን የፓን አፍሪካ ግልጽ አቋም ማሳያ መሆኑን አስረድተዋል።

የአፍሪካውያንን  የመሠረተ ልማት ፍላጎት በራስ አቅም የማሳካት ምሳሌ መሆኑን በመጥቀስ፤ ከአፍሪካ ኅብረት የአህጉራዊ የኃይል ትስስር ራዕይ ጋር የሚስማማ ነው ብለዋል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ የቀጣናው የኃይል ቋት መሆኑን ያነሱት ፕሬዝዳንቱ፤ በዚህ ወሳኝ ወቅት የአፍሪካ ቀንድ እና  የተፋሰሱ ሀገራት ዘላቂ የወንድማማችነት፣ የትብብር እና የጋራ ራዕይን ለማሳካት ተግተን እንሰራለን ነው ያሉት።

ለዚህም ኬንያ የምስራቅ አፍሪካ የኤሌክትሪክ ኃይል ወሳኝ ማዕከል ከሆነችው ኢትዮጵያ ጋር ትብብሯን አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።

ኬንያ ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል በመግዛት ትስስር መፍጠሯን አስታውሰው፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከሚያመነጨው ኃይል ለመግዛት ንግግሮች እየተደረጉ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በመላው አፍሪካ ተመሳሳይ ፕሮጀክቶችን ለማስፋት መነሻ የሆነ እና የአህጉሪቷን የኃይል አቅርቦት እጥረት ለመሙላት ትልቅ አቅም መሆኑን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስደናቂ ሥራ እየሠሩ መሆኑን ያነሱት ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ታላቁ ህዳሴ ግድብን ማሳካታቸው የህዝቦቻችንን ምኞትና ተስፋ  በትጋታችን እውን የማድረግ ሁነኛ ምሳሌ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም