ቀጥታ፡

ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ መመረቅ ለቀጣይ የልማት ስራዎች ይቻላል መንፈስን የፈጠረ  ነው

ደሴና ገንዳ ውሃ ፣ደብረ ብርሃንና ወልዲያ ፤ጳጉሜን 4/2017(ኢዜአ)፦የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ መመረቅ ለቀጣይ ልማት የይቻላል መንፈስን የፈጠረ  መሆኑን  በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች ነዋሪዎች ገለጹ።

ከደሴ ከተማ ነዋሪዎች መካከል ሼህ አብዱልዋሀብ ኑረዲን ለኢዜአ እንደገለጹት መላው ኢትዮጵያውያን የታላቁ ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ  መሰረት ከተጣለ ጀምሮ ቦንድ በመግዛትና በሌሎች አማራጮች  አስተዋጽኦ አድርገዋል።

በህዝቡ ርብርብ  ግድቡ ለምረቃ በመብቃቱ በጋራ ለመሻገር የሚያግድ ነገር እንደሌለ ማሳያ ብቻም ሳይሆን የይቻላል ወኔን በመፍጠር ኢትዮጵያውያንን የበለጠ ማስተሳሰሩን ተናግረዋል።

ተሞክሮውን በማስፋት ሌሎች ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ለመስራት በሚደረጉ ጥረቶች የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ ደሳለ ሀይሉ በበኩላቸው የአንድነት ማህተም የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተጠናቆ  በማየታቸው መደሰታቸውን ገልጸው ከተባበርን  የማናልፈው ፈተና  የለም  ብለዋል።

በምዕራብ ጎንደር ዞን የገንዳውኃ ከተማ ነዋሪው አቶ ሰጠኝ ካሴ በበኩላቸው ቦንድ በመግዛትና  ግድቡን  በአካል ቦታው ድረስ በመሄድ መጎብኘታቸውን አውስተዋል። 

ግድቡ አልቆ በማየታቸውም ኩራት እንደተሰማቸው ተናግረው ይህም የኢትዮጵያን በከፍታ ላይ የመገኘት አቅም ያሳየ መሆኑን   ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ሙስጠፋ ገደፋው ተናግረዋል። 

የግድቡ መጠናቀቅ ሀገራችን በየትኛውም ችግር  የማትናወጥ  መሆኗን ለዓለም ግልፅ ያደረገ ነው ብለዋል። 

በሌላ በኩል የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት እንዳሉት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መመረቅ አሻጋሪና ዘላቂ የልማት ግብን ለማሳካት ፋይዳው የጎላ ነው።


 

"ኢትዮጵያ ታሪኳን በልማት ቀይራ ብልጽግና እያረጋገጠች ነው" ያሉት አቶ በድሉ የግድቡ መመረቅ በከተማው እያደገ ለመጣው የኢንዱስትሪ ልማትና ኢንቨስትመንት በቂ ሃይል ለማቅረብ የሚያስችል ነው ብለዋል።

በተያያዘም የወልድያ ከተማ ነዋሪዎች የዘመናት ህልማቸው የነበረው የህዳሴ ግድብ መመረቅ ለኢትዮጵያውያን ልዩ ትንሳዔ እንደሆነ  ገልጸዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም