ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለትውልዱ ትልቅ ዕድል ይዞ የመጣ የመተባበር ምልክት ነው-የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለትውልዱ ትልቅ ዕድል ይዞ የመጣ የመተባበር ምልክት ነው-የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪዎች
ሚዛን አማን፤ጳጉሜን 4/2017(ኢዜአ)፦ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለትውልዱ ትልቅ ዕድል ይዞ የመጣ የመተባበር ምልክት መሆኑን የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።
መላውን የሀገሪቱን ህዝቦች በአንድነት ያጋመደው የሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ የማንሰራራት ዘመን ማብሰሪያ መሆኑንም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።
የግድቡን መጠናቀቅ ተከትሎ ደስታቸውን ለመግለጽ አደባባይ ከወጡ የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪዎች መካካል ወይዘሮ ብርሃኔ ታፈሰ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ የቀደምት አባቶች ምኞትና የኢትዮጵያውያን የዘመናት ህልም የነበረው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዛሬ ለፍጻሜ በቅቶ በማየታቸው የተለየ ደስታ ተሰምቷቸዋል።
ግድቡ ህዝብን በልማት ያስተሳሰረና ያጋመደ የአንድነት ማሳያ ግዙፍ ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸው፣ አትዮጵያዊያን በራስ አቅም ሰርተን ለውጤት መብቃት እንደምንችል ለዓለም ያሳየንበት በመሆኑ ኩራት ይሰማኛል ብለዋል።
በዕድሜዬ ዓባይ ለሀገር ልማት ውሎ በማየቴ የተሰማኝ ደስታ ልዩ ነው ያሉት ሌላው የከተማዋ ነዋሪና የሀገር ሽማግሌ አቶ ሀብተማርያም ካዝንቴት ናቸው።
"ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ስንነሳ ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶችንም ጀምረው መጨረስ እንደሚችሉ በተግባር ያረጋገጥንበት ነው" ብለዋል።
ግድቡ አይቻልምን ሳይሆን መቻልን በህዝብ ላይ ማስረጹን ገልጸው፣ ለዓመታት በአብሮነት የተደከመበት የልማት ፕሮጀክት ለፍጻሜ መብቃቱ ለቀጣይ ትውልድ ጭምር ኩራትና እድል መሆኑን ተናግረዋል።
ሁሉም ከልጅ እስከ አዋቂ ካለው ላይ ቀንሶ ለዓመታት ቦንድ በመግዛትና በስጦታ ለግድቡ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ያስታወሱት ደግሞ አቶ አያና ኢያሱ የተባሉ የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪ ናቸው።