የሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን አንድነትና ፅናት የታየበት አኩሪ ፕሮጀክታችን ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን አንድነትና ፅናት የታየበት አኩሪ ፕሮጀክታችን ነው
ባሕር ዳር፤ጳጉሜን 4/2017(ኢዜአ)፦ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን አንድነት፣ ፅናትና ትብብር የታየበት አኩሪ ፕሮጀክታችን ነው ሲሉ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።
ነዋሪዎቹ ግድቡ ተጠናቆ ለምረቃ በመብቃቱ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።
ከነዋሪዎቹ መካከል ወንድም ዋለልኝ ለኢዜአ እንዳሉት፣ ዛሬ ለመላው ኢትዮጵያውያን አዲስ የተስፋ ብርሃን የፈነጠቀበት ልዩ ቀን ነው።
የግድቡን ፍፃሜ በጉጉት እንጠብቀው ነበር ያሉት ነዋሪው፤ በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፎ የመጠናቀቁን ዜና በሰሙበት ወቅት ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ተናግረዋል።
ለግድቡ ግንባታ መሳካት በልጃቸውም ሆነ በራሳቸው ስም ቦንድ በመግዛት አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን አስታውሰው፤ ፍሬውን ማየት በመቻላቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።
ግድቡ የመላው ኢትዮጵያውያን አንድነት፣ ትብብር፣ ሕብረትና ፅናት የታየበት አኩሪ ፕሮጀክታችን ነው ብለዋል።
ታላቁ የሕዳሴ ግድብ መስዋእትነት ጭምር ተከፍሎበት ለውጤት የበቃና የመሪዎች ቆራጥነት የተረጋገጠበት ስኬት መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ወይዘሮ አታሌ ነጮ ናቸው።
ለግድቡ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ከተቀመጠበት ጊዜ ጀምሮ የገንዘብ መዋጮ እንዳደረጉና በመጠናቀቁ ኩራት እንደተሰማቸው ገልጸዋል።
ሌላው የከተማው ነዋሪ ዳዊት ሞት ባይኖር በበኩላቸው፤ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የአይቻልምን መንፈስ የሰበረና የይቻላልን ጉልበት የጨመረ ፕሮጀክት ሲሉ ተናግረዋል።
በዚሕም የኢትዮጵያ ሕዝብ ትብብርና አንድነት እንዲሁም ለሃገር ፍቅርና ልማት ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር ማሳየት ያስቻለ እንደሆነ አብራርተዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን ከፍታና የስልጣኔ ቀደምትነትን የደገመ ነው ብለዋል።