ቀጥታ፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የስራ ኃላፊዎች የክብር ኒሻን አበረከቱ

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 4/2017(ኢዜአ)፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የስራ ኃላፊዎች የክብር ኒሻን አበርክተዋል።

በኢትዮጵያዊያን ገንዘብ፣ የላብ እና የደም ጠብታ እውን የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተጠናቆ ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተመርቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በግድቡ ግንባታ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ዜጎች የክብር ኒሻን አበርክተዋል።

በዚህም መሰረት ኢንጂነር ኤፍሬም ወልደኪዳን ከሕዳር 24 ቀን 2004 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ጥር 14 ቀን 2017 ድረስ ሃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ምክትል ስራ አስኪያጅ ሆነው በማገልገላቸው ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የክብር ኒሻን ተበርክቶላቸዋል።

በቀጣይ ኢንጂነር ከማል አሕመድ ሌላኛው የክብር ኒሻን የተበረከተላቸው ሲሆን ከሚያዚያ 2013 ዓ.ም ጀምሮ እስከ አሁን የግድቡ ግንባታ የኦፕሬሽን ስራ አስኪያጅ ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ።

አቶ በላቸው ካሳ የግድቡ ግንባታ ፕሮጀከት በምክትል ስራ አስኪያጅነት ማእረግ የሳይት አስተባባሪ ሆነው እያገለገሉ የሚገኙ ሲሆን የክብር ኒሻናቸውን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ተረክበዋል።

በመጨረሻም ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ የታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድቡ ግንባታ ፕሮጀክት ዋና ስራ አስኪያጅ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የክብር ኒሻን ተቀብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም