የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አፍሪካ የራሷን እጣ ፈንታ በራሷ የመወሰን አቅም እንዳላት የሚያሳይ ታላቅ ፕሮጀክት ነው-ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ - ኢዜአ አማርኛ
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አፍሪካ የራሷን እጣ ፈንታ በራሷ የመወሰን አቅም እንዳላት የሚያሳይ ታላቅ ፕሮጀክት ነው-ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ

አዲስ አበባ፤ጳጉሜን 4/2017(ኢዜአ)፦ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አፍሪካ የራሷን እጣ ፈንታ በራሷ የመወሰን አቅም እንዳላት የሚያሳይ ታላቅ ፕሮጀክት ነው ሲሉ የኬንያ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ገለጹ።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በዛሬው ዕለት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ተመርቋል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፣ የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ (ዶ/ር)፣ የጂቡቲው ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦመር ጊሌህ፤የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ (ዶ/ር) ፤የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር ማያርዲት፤የባርባዶስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚያ አሞር ሞትሊ፤የእስዋቲኒ ጠቅላይ ሚኒስትር ሩሴል ሚሶ ድላሚኒ፤የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር መሀመድ አሊ ዩሱፍ፤ በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ፀሐፊ ክላቨር ጋቴቴ ተገኝተዋል።
በተጨማሪም፣የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ፤የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር ፤ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ተገኝተዋል።
የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ባደረጉት ንግግር፥የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ምርቃት ትልቅ ታሪካዊ አንድምታ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ህዝብ እና መንግስት ለዚህ ታሪካዊ ስኬት ስለበቃችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት እወዳለሁ ብለዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የምህንድስና ስራ ሳይሆን አፍሪካ የራሷን መጻኢ እድል በራሷ መወሰን እንደምትችል የሚያሳይ ነው ብለዋል።
አፍሪካውያን የራሳቸውን የብልጽግና መሻት በራሳቸው ማካሳት እንደሚችሉም የሚያመላክት መሆኑን ተናግረዋል።
ይህን ታላቅ ታሪካዊ ቀን እያከበርን ባለንበት ወቅት የአፍሪካ ቀንድ እና የናይል ተፋሰስ ሀገራት ለጋራ ትብብር ያለንን ቁርጠኝነት በግልጽ እያሳየን ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ኬንያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር በቁርጠኝነት እንደምትሰራ ገልጸው፥ ኢትዮጵያ በቀጣናው ቁልፍ ሚና የምትጫወት ሀገር ናት ብለዋል።
ኢትዮጵያ በኢነርጂ ራሷን ለመቻል እና ኢኮኖሚዋን ለመለወጥ እያደረገች ያለውን ለውጥ አድንቀዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ከብሄራዊ ፕሮጀክትነት ባለፈ የፓን አፍሪካ አቅምን በተግባር ያሳየና የአፍሪካ መር መሰረተ ልማት ግንባታ መገለጫ መሆኑን ተናግረዋል።
ግድቡ በቀጣናው ለሰላም እና ብልጽግና ያለንን የጋራ ህልም ማሳካት በእጃችን ያለ ጉዳይ መሆኑን የሚያሳይ እንደሆነ ተናግረዋል።
ህዝባችንን ለመቀየር እና የኑሮውን ሁኔታ ለማሻሻል በመተባበር መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።