ታላቁ የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን አብሮነት እና መተባበር ማሳያ ነው -የኦሮሚያ ክልል ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን አብሮነት እና መተባበር ማሳያ ነው -የኦሮሚያ ክልል ነዋሪዎች
ነገሌ ቦረና/ጊምቢ/አምቦ ፤ጳጉሜን 4/2017(ኢዜአ)፦ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን አብሮነትና መተባበር ማሳያ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ከተሞች ነዋሪዎች ገለጹ።
በኦሮሚያ ክልል ነገሌ ቦረና፣ ጊምቢ እና አምቦ ነዋሪዎች ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መመረቁን በማስመልከት ደስታቸውን በተለያየ መልኩ ገልጸዋል።
ደስታቸውን ለመግለጽ አደባባይ ከወጡ የነገሌ ቦረና ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ ብርሀኑ አበበ፣ የግድቡ መመረቅ ኢትዮጵያዊ አንድነት፣ አብሮነትና ትብብር የታየበት መሆኑን ገልጸዋል።
አካል ጉዳተኝነታቸው ሳይገድባቸው በሊስትሮ ስራ እንደሚተዳደሩ ገልጸው ባለፉት ዓመታት በሶስት ዙር ቦንድ በመግዛት ድጋፍ ማድረጋቸውንና ግድቡ ተጠናቆ ለምረቃ በመብቃቱ ደስታቸውን ለመግለጽ ወደ አደባባይ እንደወጡም ገልጸዋል፡፡
ሌላው የከተማው ነዋሪና የመንግስት ሰራተኛው አቶ ሲሳይ ማሄ፤ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በ4 ዙር ቦንድ መግዛታቸውን አስታውሰዋል፡፡
''ግድቡ ለምረቃ በመብቃቱ ኮርቻለሁ፤ ፕሮጀክቱ የብልጽግና ጉዞን የሚያፋጥን ታሪካዊ ድልና ስኬት በመሆኑ ሁላችንንም ለበለጠ ስራ የሚያነሳሳ ነው'' ብለዋል፡፡
''ከተባበርን ከራሳችን አልፎ ለሌሎችም የሚተርፍ ተአምር የመስራት አቅምና ብቃት እንዳለን በታላቁ ህዳሴ ግድብ አሳይተናል'' ሲሉም ተናግረዋል።
ታላቁ የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን ህብረት፣ አንድነትና የመቻል አቅም የታየበት ነው ያሉት ደግሞ የከተማው ነዋሪ አቶ ግርማ አሊ ናቸው።
''የግድቡ መመረቅ ዳግማዊ አድዋ በመሆኑ ኩራት ይሰማኛል፣ ለቀጣይ ድልና ስኬት በአብሮነት ለመስራት መንገድ የሚጠርግ ነው'' ብለዋል፡፡
በተመሳሳይም የምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ከተማ ነዋሪዎችም ታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቅቆ ለምርቃት በመብቃቱ ትልቅ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል።
የግድቡ መጠናቀቅ በሌሎች የልማት ዘርፎች ውጤታማ ስራ ለመስራት የሚያነሳሳ መሆኑን አንስተው ከፍተኛ መነሳሳት እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።
የአምቦ ከተማ ነዋሪዎችም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቅቆ መመረቁ ሁለተኛው የአድዋ ድል ነው ሲሉም አስረድተዋል።
የከተማው እና አካባቢው ነዋሪዎች የህዳሴ ግድብ መመረቁን በተመለከተ ደስታቸውን በሰላማዊ ሰልፍ እና በጎዳና ላይ ትርዒት ገልጸዋል።