ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የአንድነት እና የመስዋዕትነት ምልክት ነው - የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር ማያርዲት - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የአንድነት እና የመስዋዕትነት ምልክት ነው - የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር ማያርዲት
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 4/2017(ኢዜአ)፡- ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የአንድነት እና የመስዋዕትነት ምልክት ነው ሲሉ የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር ማያርዲት ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን መርቀዋል።
በክብር እንግድነት የተገኙት የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር ማያርዲት ባስተላለፉት መልዕክት በዚህ ታሪካዊ ዕለት በመገኘታቸው በደቡብ ሱዳን መንግስትና ህዝብ ስም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ለኢትዮጵያውያንም የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ብለዋል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ብቻ ሳይሆን የአንድነትና የመስዋእትነት ምልክት ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የግድቡ ግንባታ እውን መሆን ህዝብ ከተባበረ እና ለአንድ ዓላማ በአንድነት ከቆመ ምን መስራት እንደሚችል ማሳያ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
ዛሬ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ የኩራት ቀን ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ ግድቡ የኃይል ፍላጎትን ከማሳካት ባለፈ ለልጆቻችን የምንመኘውን የበለጸገ ሀገርና አህጉር ለማስረከብ እድል የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡
ደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ ጎረቤት ብቻ ሳትሆን ለኢትዮጵያውያን ወንድምና እህቶች ነን ያሉት ፕሬዝዳንቱ የጋራ ታሪክና ወዳጅነት እንዲሁም የጋራ ህልም ያለን ሀገራት በመሆናችን በዛሬው ቀን እዚህ ተገኝተናል ነው ያሉት፡፡
የአንድ ሀገር እድገት የሁሉም ሀገር እድገት መሆኑን በመግለጽም ለሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ለብልጽግና በትብብር እንሰራለን ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅን ተከትሎ ደቡብ ሱዳን የኤሌክትሪክ ኃይል ለማግኘት ከኢትዮጵያ ጋር አዲስ ስምምነት ለመፈረም እቅድ እንዳላትም ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል፡፡
ይህም ለደቡብ ሱዳናውያን ትልቅ እድል መሆኑን ጠቁመው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ብልጽግናን እንደሚያመጣ ያላቸውን እምነትም ገልጸዋል፡፡