ቀጥታ፡

በህዳሴ ግድብ ላይ የተገኘውን ውጤት በሌሎች የልማት መስኮች ለመድገም እንረባረባለን

ሮቤ፤ ጳጉሜን 4/2017(ኢዜአ):-በህዳሴ ግድብ ላይ የተገኘውን ውጤት በሌሎች የልማት መስኮች ለመድገም እንረባረባለን ሲሉ የባሌ ዞን የአጋርፋ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ። 

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መመረቁን አስመልክቶ በባሌ ሮቤና ሌሎች  የዞኑ ወረዳዎች የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ያሳተፈ የድጋፍ ሰልፍ እየተካሄደ ይገኛል።

በአጋርፋ ወረዳ የድጋፍ ሰልፉ ተሳታፊዎች በታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ላይ የተገኘውን ውጤት በሌሎች መስኮች ላይም ለመድገም እንረባረባለን ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። 

ከነዋሪዎቹ መካከል ሼህ ሁሴን አህመድ በሰጡት አስተያየት የታላቁ የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን የላብ አሻራ ያረፈበት የአብሮነትና የአንድነት ፕሮጀክት ነው ብለዋል። 


 

ታላቁ የህዳሴ ግድብን በማጠናቀቅ የተገኘውን ስኬት በሌሎች የልማት ፕሮጀክቶች ላይ ለመድገም እንደሚረባረቡ ተናግረዋል። 

ለግድቡ ግንባታ ቦንድ በመግዛት ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ያስታወሱት ደግሞ ወይዘሮ ከበቡሽ ገረሱ ናቸው። 


 

የህዳሴ ግድቡ በርካታ ፈተናዎችን ተሻግሮ የምረቃውን ዜና በመስማታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።

ህዳሴ ግድቡ ግንባታ ፍጻሜ አንድነትና መተባበር ለስኬት እንደሚያበቃ ያየንበት የታሪክ አጋጣሚ ነው ያሉት ደግሞ አብደላ ሱልጣን ናቸው። 


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም