ቀጥታ፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ  የሀገራችን የንጋት ዘመን አብሳሪ ነው-ደረጀ እንግዳ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ጳጉሜን 4/2017(ኢዜአ)፦ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ  በአንድነት ጠንክሮ በመሥራት የተሳካ የንጋት ዘመን አብሳሪ ድል መሆኑን የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ደረጀ እንግዳ (ዶ/ር) ገለፁ። 

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ  በህብረት እውን የሆነ የኢትዮጵያ የማንሰራራት ዘመን መገለጫና  የመቻል ማሣያም ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያውያን በራሳቸው አቅም የገነቡትን ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በዛሬው ዕለት በይፋ መርቀዋል።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ደረጀ እንግዳ (ዶ/ር) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ   የሀገራችንን የብርሃን ጉዞ ያበሰረ ነው ብለዋል።


 

የግድቡ ሀይቅ ስያሜ “ንጋት” ተብሎ መሰየሙ ሀገራችን አሁን ያለችበትን የእድገት ጉዞና የንጋት ዘመን ማብሰሪያ መሆኑንም ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በፕሮጀክቱ ላይ ያሳዩት የአመራር ጥበብ ሁሉም ዜጋ በየተሰማራበት የስራ ዘርፍ ልምድ የሚወስድበት እንደሆነ ነው የተናገሩት።

ግድቡ የሀገራችንን ትልቅነት የምናስመሰክርበትና በጋራ ከቆምን ማንኛውንም ፈተና አልፈን ብልፅግናችንን ማረጋገጥ እንደምንችል ያሳየንበት ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን ካላቸው ላይ ቀንሰው እውን ያደረጉት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የአንድነት አርማችን ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያውያን ከጫፍ ጫፍ በአንድነት ያሳኩት የድል አድራጊነት ምልክት በመሆኑ ሁለተኛው ዓድዋ ነው ሲሉ ገልጸውታል፡፡

አንድነታችንን ማጠናከር ለብልጽግናችን ወሳኝ መሆኑን በግድቡ አሳይተናል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም