የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ አንድነታችን እና መተባበራችን ያስገኘው ውጤት ነው -የጅማ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ አንድነታችን እና መተባበራችን ያስገኘው ውጤት ነው -የጅማ ከተማ ነዋሪዎች
ጅማ፤ጳጉሜን 4/2017(ኢዜአ)፦ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ አንድነታችን እና መተባበራችን ያስገኘው ውጤት ነው ሲሉ የጅማ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።
የጅማ ከተማ ነዋሪዎች ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተጠናቆ በመመረቁ ደስታቸውን በከተማዋ ዋና ዋና መንገዶች በመዘዋወር ገልጸዋል።
በዚሁ ጊዜ ኢዜአ ያነጋገራቸው የከተማው ነዋሪዎች ታላቁ የህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ አንድነታችንና መተባበራችን ያመጣው ውጤት በመሆኑ ፍጻሜውን በማየታችን ተደስተናል ብለዋል።
ከነዋሪዎቹ መካከል ወይዘሮ አሚና አባ ነጋ፤ የግድቡ መጠናቀቅ ትልቅ የደስታ ስሜት ያለው በመሆኑ ስሜታችንን ለመግለጽ አደባባይ ወጥተናል ብለዋል።
በርካታ ፈተናዎችና ውጣ ውረዶችን አልፎ እዚህ የደረሰው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን ትልቅ ተስፋና የጥንካሬያችን ማሳያ ነውም ብለዋል።
ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ብርቱካን ዜይኑ፤ ይህ ትልቅ ፕሮጀክት የመላው ህዝባችን አንድነት የታየበት የትብብራችን ምልክት ነው ብለዋል።
የጅማ ከተማ ከንቲባ ጣሃ ቀመር በበኩላቸው የሁላችንም የጥረትና የቁርጠኝነት ውጤት የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በመጠናቀቁ ሁላችንም ተደስተናል ብለዋል።
በህዳሴ ግድብ ግንባታ ሁሉም የተሳተፈበትና በራስ አቅም ግዙፍ ፕሮጀክት መስራት እንደምንችል ያሳየንበት ፈተናዎችን ተቋቁመን ማሸነፍ የቻልንበት ነው ሲሉም ተናግረዋል።