ቀጥታ፡

የህዳሴ ግድብ እውን መሆን ለሌሎች ታላላቅ የልማት ስራዎች አነሳስቶናል - የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች

አሶሳ፤ ጳጉሜ 04/2017 (ኢዜአ)፦ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለምርቃት መብቃቱ ለሌሎች ታላላቅ  የልማት ተግባራት መነቃቃት እንደፈጠረላቸው የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

የዘመናት ቁጭት የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተጠናቆ ለምረቃ መብቃቱን አስመልከቶ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ታላቅ ደስታ እንደተሰማው በመግለጽ ላይ ይገኛል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማም የግድቡን ምረቃ  አስመልክቶ ነዋሪው የጎዳና ላይ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ደስታውን ገልጿል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎችም የግድቡ መጠናቀቅ ደስታ እንደፈጠረባቸውና በቀጣይ ሌሎች ታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ለመስራት መነቃቃት እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል።

ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ አንዋር አስር እንዳሉት ግድቡ የኢትዮጵያዊያንን የመፈጸም አቅም ያሳየ እና ለሌላ ፕሮጀክት አቅም የፈጠረ ነው።


 

በግድቡ ግንባታ በምንጣሮ ስራ መሳተፋቸውን ገልፀው ግድቡ ለምርቃት መብቃቱ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል።

አቶ ሱሌማን ሙሳ እንዳሉት ህዳሴ ግድቡ የኢትዮጵያውያን የልፋት ውጤት በመሆኑ ሁላችንም ተደስተናል።


 

የግድቡ ውሃ የሚይዝበት ቦታ የደን ምንጣሮ ላይ መሳተፋቸውን የገለፁት አቶ ሱሌማን የልፋቴን ውጤት በማየቴም ልዩ ደስታ ተሰምቶኛል ብለዋል።

ኢንስፔክተር ጀማል ቃሲም በበኩላቸው የግድቡ ምርቃት ዋዜማ ጀምሮ የተለየ ደስታ ስሜት እንደተሰማቸው ገልጸዋል።


 

ግድቡ ኤሌክትሪክ ከማመንጨት ባለፈ ለወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር ታላቅ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም