የሕዳሴው ግድብ ለምረቃ መብቃቱ የኢትዮጵያን የማንሰራራት ዘመን እውን ለማድረግ መነሳሳትን የሚፈጥር ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሕዳሴው ግድብ ለምረቃ መብቃቱ የኢትዮጵያን የማንሰራራት ዘመን እውን ለማድረግ መነሳሳትን የሚፈጥር ነው
ጎንደር/ ደብረ ማርቆስ ፤ጳጉሜን 4/2017(ኢዜአ)፦ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቆ ለምረቃ መብቃቱ የኢትዮጵያን የማንሰራራት ዘመን እውን ለማድረግ መነሳሳትን የሚፈጥር መሆኑን የጎንደር እና ደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
ቦንድ በመግዛት፣ በገንዘብና ሌሎች ድጋፎችን በማድረግ ግድቡ ተጠናቆ ለምረቃ እንዲበቃ ያደረግነው አስተዋጽኦ ዛሬ ፍሬውን በማየታችን ተደስተናው ሲሉ ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።
የጎንደር ከተማ ነዋሪ አቶ አድማሴ ደሞዝ ፤ በሕይወት እያለሁ ግድቡ ተጠናቆ ለምረቃ በቅቶ በማየቴ ደስታዬ ወደር የለውም ብለዋል።
የሕዳሴው ግድብ የኢትዮጵያውያን መሪዎች የአመራር ጥበብና ቆራጥ ውሳኔ ማሳያ ነው ያሉት አቶ አድማሴ፤ የሕዝባችንም የዘመናት ቁጭት የወለደው አኩሪ ታሪካዊ ተግባር ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ሌላው የከተማዋ ነዋሪ መላእከ ገነት ቄስ ፈንታ ገብረሚካኤል በበኩላቸው፤ የሕዳሴው ግድብ የመላው ሕዝብ ትጋትና የአንድነታችን መገለጫ በመሆኑ ለምረቃ በመብቃቱ ደስታዬ ወደር የለውም ብለዋል።
የሕዳሴው ግድብ ኢትዮጵያውያንን ከጨለማ ወደ ብርሃን ያሸጋገረ የዚሕ ትውልድ አሻራና ማሕተም ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል የደብረማርቆስ ከተማ የቀበሌ 10 ነዋሪ አቶ አዱኛ ተሰማ ፤ የሕዳሴ ግድቡ ለምረቃ መብቃት ደስታው ወደር እንደሌለው ተናግረዋል።
በቀጣይም የግድቡ መጠናቀቅ የፈጠረልንን መነሳሳት በመጠቀም ትልልቅ ፕሮጀክቶችን በጋራ በመገንባት የበለጸገች ሀገር እንደምንፈጥር እርግጠኛ ነኝ ሲሉ ገልጸዋል።
ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አቶ አዝመራው ባወቀ በበኩላቸው፤ የሕዳሴው ግድብ መመረቅ በቃላት ከሚገልጹት በላይ እንደሆነባቸው ተናግረዋል።
ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ለስኬት መብቃቱ የኢትዮጵያን የማንሰራራት ዘመን እውን ለማድረግ መነሳሳትን የሚፈጥር አኩሪ ተግባር መሆኑን አስተያየት ሰጪዎቹ ገልጸዋል።