ቀጥታ፡

የሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያዊያንን ለአንድ ዓላማ ያሰለፈ የአብሮነት አርማችን ነው-የጂንካ ከተማ ነዋሪዎች 

ጂንካ ፤ጳጉሜን 4/2017(ኢዜአ)፦ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያዊያንን ከያሉበት በማነቃነቅ ለአንድ ዓላማ ያሰለፈ የአብሮነት አርማችን ነው ሲሉ የጂንካ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

በግደቡ መጠናቀቅ የጂንካ ከተማ ነዋሪዎች ደስታቸውን እየገለጹ ነው።

የግድቡ መጠናቀቅን አስመልክቶ ደስታቸውን ለኢዜአ ከገለጹት የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል መምህር ተስፋዬ ረታ የሕዳሴው ግድብ ኢትዮጵያውያንን ከጫፍ ጫፍ በማነቃነቅ ለልማት በአንድነት ያቆመ ነው።


 

ግድቡ የኢትዮጵያዊያን ብሔራዊ አርማችን ነው ያሉት መምህሩ ልዩነትን አጥብቦ ህዝብን ለአንድ ዓላማ ያሰለፈው የሕዳሴ ግድብ ዛሬ ለምረቃ በመብቃቱ የተለየ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያዊያን በተባበረ ክንድ በየትውልዱ ሲታወስ የሚኖር ደማቅ ታሪክ ሰርተናል ያሉት መምህሩ የግድቡ መጠናቀቅ ለሀገርና ለህዝብ መልካም እድሎችን ይዞ ይመጣል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሰጡት በሳል አመራር ግድቡ ተጠናቆ ለምረቃ በመብቃቱ ምስጋና ይገባቸዋል፤ ታሪክም ሲያወሳቸው ይኖራል ብለዋል።

"ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን እንደበኩር ልጄ ነው የማየው" በማለት አስተያየታቸውን በደስታ ስሜት የገለጹት ደግሞ ሌላው የጂንካ ከተማ ነዋሪ ባሻ ፀጋዬ ታደሰ ናቸው።


 

በመንግሥት ሥራ ሳሉ እስከ ጡረታ መውጫ ጊዜያቸው ድረስ ለ14 ዓመታት ቦንድ በመግዛት ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

"በቀረኝ የጡረታ ዕድሜ ግድቡ ተጠናቆ በማየቴ ልገልፀው የማልችለው ደስታ ተሰምቶኛል" ሲሉም የተሰማቸውን ስሜት ሳግ እየተናነቃቸው ገልጸዋል።

ግድቡ እንደህዝብ በአንድነት ለመቆም አነሳስቶናል ያሉት ባሻ ፀጋዬ፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን አሻራችንን በማሳረፍ ደማቅ ታሪክ የጻፍንበት ግድብ ተጠናቆ ዛሬ በመመረቁ የተለየ ደስታ ተሰምቶኛል ብለዋል።  

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለፍጻሜ መብቃት በሀገራችን ያለንን ተስፋ አለምልሞታል ያለው ደግሞ ወጣት ሽመልስ ተስፋዬ ነው።


 

ብሔራዊ አርማችን የሆነው የሕዳሴ ግድብ በተባበረ ክንድ ተገንብቶ መጠናቀቁ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ከተነሳን የማናሳካው ነገር እንደማይኖር ማሳያ ነው ብሏል።

በሕዳሴ ግድብ ያሳየነው ፍቅር፣ አንድነት፣ ጽናትና ታታሪነት በሌሎች ልማቶችም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

"አይችሉም፤ አይሳካላቸውም ሲሉን ለነበረ ሁሉ እንደምንችል ለዓለም ህዝብ ያሳየንበት የኢትዮጵያዊያን የአብሮነት ውጤት የሆነው ግድብ ዛሬ ተጠናቆ በመመረቁ ደስታዬ ወደር የለውም" ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ፀሐይ ተስፋዬ የተባሉ ነዋሪ ናቸው። 


 

የመላው ኢትዮጵያዊያን የ14 ዓመት ልፋትና ጥረት ለፍሬ በመብቃቱ  ለሌላ ልማት በጋራ እንድንነሳሳ የሚያደርግ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

ላለፉት ዓመታት የተለያዩ ውጣ ውረዶችን በማለፍ በኢትዮጵያዊያን ብርቱ ክንድ የተገነባውና ዛሬ የተመረቀው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ካለው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ባለፈ ኢትዮጵያን ከሌሎች ሀገራት ጋር በልማት የማስተሳሰር ግብ አለው።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም