ቀጥታ፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ አንድነታችንን ያጠናክራል

አዲስ አበባ፤ጳጉሜን 4/2017(ኢዜአ)፦ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ አንድነትን ያጠናከረ እና የይቻላል መንፈስ የፈጠረ መሆኑን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የመዲናዋ ወጣቶች ገለጹ፡፡

በኢትዮጵያዊያን ገንዘብና የላብ አሻራ እውን የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተጠናቆ ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተመርቋል።

የህዳሴ ግድብ  መጠናቀቅን አስመልክቶ ኢዜአ ያነጋገራቸው የመዲናዋ ወጣቶች እንዳሉት፤የህዳሴ ግድብ ተጠናቆ ለምረቃ መብቃቱ ለኢትዮጵያውያን ትልቅ ብስራት ነው፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በርካታ ውጣ ውረዶችንና ፈተናዎችን አልፎ ለምረቃ በመብቃቱ መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡

ግድቡ ከተጀመረ ጀምሮ በገንዘብና በጉልበት እንዲሁም ቦንድ በመግዛት ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡

ወጣት አብርሃም አበራ እንደሚለው፤ የግድቡ እውን መሆን ኢትዮጵያን በኢኮኖሚ ዘርፍ ወደፊት የሚያራመድ ነው፡፡


 

አቶ ተስፋዬ እያዩ በበኩላቸው፤ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን እውን ለማድረግ ቦንድ በመግዛት፣ በሃሳብና በጉልበት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደተወጡ ገልጸዋል፡፡

አሁን ላይ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት መጠናቀቅ  ለኢትዮጵያ  ትልቅ ብስራት መሆኑን በመግለጽ፤ ለወደፊትም መሰል ፕሮጀክቶችን ለማሳካት ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል።  


 

ወጣት ማህደር ሃይሌ በበኩሏ ፤የእሷና የመላ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውዊያን ድጋፍ ታክሎበት የህዳሴ ግድብ ግንባታ በመጠናቀቁ ትልቅ ደስታ እንደተሰማት ገልጻለች፡፡


 

አቶ ኦፍታና ሂንደቡ ከግንባታው ጅማሮ አንስቶ በተለያየ መልኩ ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሰው ሁሉም ኢትዮጵያዊ የተሳተፈበት ፕሮጀክት እውን በመሆኑ መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም