ኢትዮጵያ ያሏትን እምቅ የተፈጥሮ ሃብቶች በማልማት እያንሰራራች ትገኛለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ያሏትን እምቅ የተፈጥሮ ሃብቶች በማልማት እያንሰራራች ትገኛለች
አዲስ አበባ፤ጳጉሜን 4/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ያሏትን እምቅ የተፈጥሮ ሃብቶች በማልማት እያንሰራራች ትገኛለች ሲሉ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የካቢኔ ጉዳዮችና ሴክተሮች ክትትል ሚኒስትር ዴኤታ አክሊሉ ታደሰ ገለፁ።
ጳጉሜን 4 የማንሰራራት ቀን “ዘላቂ ልማት ለሀገራዊ ማንሰራራት " በሚል መሪ ሐሳብ በመላው ሀገሪቱ እየተከበረ ይገኛል፡፡
ቀኑን አስመልክቶ የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞ ከአዲስ አበባ ጅቡቲ በሚጓዘው ባቡር ውስጥ “የማንሰራራት ጉዞን በጉዞ” በሚል መሪ ሃሳብ ውይይት ተካሂዷል፡፡
በውይይቱም ባለፈው ዓመት በታላቁ ህዳሴ ግድብ፣ በኢንዱስትሪ፣ በሌማት ትሩፋት፣ በአረንጓዴ አሻራ፣ በኮሪደር ልማት፣ በገበታ ለትውልድ እና በመደመር ትውልድ ፕሮጀክቶች የታዩ ውጤታማ ስራዎች የኢትዮጵያ የማንሰራራት ማሳያዎች መሆናቸው ተገልጿል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የካቢኔ ጉዳዮችና ሴክተሮች ክትትል ሚኒስትር ዴኤታ አክሊሉ ታደሰ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ባለፉት የለውጥ አመታት የኢትዮጵያን ማንሰራራት የሚያበስሩ ውጤቶች ተመዝግበዋል።
በግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነት ማሳደግ የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎች መጠቀም የተቻለበት እንደሆነም ተናግረዋል።
በሌማት ትሩፋት፣ በስንዴ፣ በአቮካዶ ልማት አበረታች ውጤት መመዝገቡን አንስተው ከራስ አልፎ ወደ ውጭ መላክ የታቻለበት ነው ብለዋል።
በሁሉም መስኮች ያሉ ሀብቶችን አሟጦ ተጠቅሞ ኢትዮጵያን የማበልፀግ ጉዞ ሊቀለበስ በማይችል ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ እያደረገች ባለችው የማንሰራራት ጉዞ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የበኩሉን አስተዋፅኦ እያበረከተ እንዳለ አንስተው ይህ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር አክስዮን ማህበር ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በበኩላቸው፤ ባለፉት የለውጥ አመታት በተከናወኑ የለውጥ ስራዎች ተቋዳሽ ከሆኑ ተቋማት መካከል የኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር አክስዮን ማህበር አንዱ ነው ብለዋል።
አክስዮን ማህበሩ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እንዲያንሰራራ በሎጂስቲክስ ዘርፉን በማሳለጥ አስቻይ ሁኔታዎች እየተጫወተ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በዚህ የማንሰራራት ዘመን የግሉ ዘርፍ እየተጫወተ ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑንም አንስተዋል።