በህዳሴ ግድብ ያስመዘገብነውን ስኬት በሌሎች መስኮች ላይ ለመድገም እንረባረባለን - ኢዜአ አማርኛ
በህዳሴ ግድብ ያስመዘገብነውን ስኬት በሌሎች መስኮች ላይ ለመድገም እንረባረባለን
ወልቂጤ ፤ጳጉሜን 4/2017(ኢዜአ)፦ ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን በማጠናቀቅ ያስመዘገብነውን ስኬት በሌሎች የልማት መስኮች ላይ ለመድገም እንረባረባለን ሲሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ነዋሪዎች ገለጹ።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅን አስመልክቶ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ነዋሪዎች የጋራ የልማት አቅሞችን በመጠቀም ለኢትዮጵያ ብልፅግናና ማንሰራራት ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የዱራሜ ከተማ ነዋሪው አቶ ደመቀ ላሜቦ የአብሮነትና የአንድነት መገለጫ የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ትውልዱ የሚኮራበት ታሪካዊ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።
ለግድቡ ግንባታ ቦንድ በመግዛትና በሌሎች አማራጮች የድጋፍ ተሳትፎ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አንስተው ግንባታው ተጠናቅቆ የምረቃውን ዜና በመስማታቸው መደሰታቸውን ጠቁመዋል።
ከህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ በተማርነው በትብብር የመፈፀም ተሞክሮን ይዘን ሌሎች ትላልቅ ፕሮጀክቶችን ገንብቶ ለማጠናቀቅ በየተሰማራንበት መስክ የሚጠበቅብንን ለመወጣት ዝግጁ ነን ብለዋል።
እናቶች ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከመቀነታቸው በመፍታት ያደረጉት ተሳትፎ የሚደነቅ ነው ያሉት ደግሞ በጉራጌ ዞን የወልቂጤ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ትብለጥ ኢስጢፋኖስ ናቸው ።
ኢትዮጵያውያን በብዝሃነት ውስጥ ጠንካራ አንድነት በማጎልበት ለሀገራቸው ትጋት ያሳዩበት ነውም ብለዋል ።
ስለሆነም አንድነታችንን በማስጠበቅ የጀመርነውን የብልጽግና ጉዞና የሀገሪቱን ማንሰራራት ለማረጋገጥ መስራት እንደምንችል ህዳሴ ማሳያ ነው ብለዋል ወይዘሮ ትብለጥ።
የህዳሴ ግድብ ግንባታን በተቀናጀ ትብብርና ድጋፍ አሳክተናል ያሉት ወይዘሮ ትብለጥ ይህም ሌሎች ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ የበለጸገች ሀገርን ለትውልድ ለማሸጋገር ጉልበት ይሆነናል ሲሉም ተናግረዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ መነቴ ሙንዲኖ የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ለማጠናቀቅ ህብረተሰቡ ያደረገውን ርብርብ አስታውሰዋል።
ዜጎች የሀገራቸውን ከፍታ ለማየት ያላቸውን ጉጉት ታላቁ የህዳሴ ግድብን በማጠናቀቅ አሳይተዋል ብለዋል።
የህዝቡ የልማት ርብርብና የመንግስት የውጭ ጫናን የመቋቋም ብቃት ግድቡ ከግብ እንዲደርስ ማድረጉን አንስተዋል።
በህዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት የታየውን አንድነት በሌሎች ትልልቅ የልማት ስራዎች ላይም በመድገም ለኢትዮጵያ ማንሰራራትና ብልፅግና ይበልጥ መስራት ይገባል ብለዋል።