ቀጥታ፡

መንግስት የኢትዮጵያን ማንሰራራት እውን የሚያደርጉ በርካታ አዳዲስ መዳረሻዎችን ከማልማት ባሻገር ነባሮቹንም አድሷል 

አዲስ አበባ፤ጳጉሜን 4/2017(ኢዜአ)፦መንግስት ለቱሪዝም በሰጠው ትኩረት የኢትዮጵያን ማንሰራራት እውን የሚያደርጉ በርካታ አዳዲስ መዳረሻዎችን ከማልማት ባሻገር ነባሮቹንም የማደስ ተግባራት ማከናወኑ ተገለጸ፡፡

ጳጉሜን 4 የማንሰራራት ቀን " ዘላቂ ልማት ለሀገራዊ ማንሰራራት " በሚል መሪ ሀሳብ በመላው ሀገሪቱ እየተከበረ ይገኛል፡፡  

2017 በጀት ዓመት ኢትዮጵያ ከነበሩባት ማነቆዎች በመላቀቅ ታሪክ ቀያሪ ድሎችን ማስመዝገብ የጀመረችበት ዓመት ነው።  

የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞ ከአዲስ አበባ ጅቡቲ በሚጓዘው ባቡር ውስጥ የማንሰራራት ጉዞን በጉዞ በሚል መሪ ሀሳብ ውይይት ተካሂዷል፡፡ 


 

በውይይቱም ባለፈው ዓመት በታላቁ ህዳሴ ግድብ፣ በኢንዱስትሪ፣ በሌማት ትሩፋት፣ በአረንጓዴ አሻራ፣ በኮሪደር ልማት፣ በገበታ ለትውልድ እና በመደመር ትውልድ ፕሮጀክቶች የታዩ ውጤታማ ስራዎች የኢትዮጵያ የማንሰራራት ማሳያዎች ናቸው ተብሏል። 

ባለፉት ዓመታት በቱሪዝምና ሆቴል ዘርፍ የተከናወኑ ውጤታማ ተግባራት አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡት የዓለም አቀፍ ሆቴልና ቱሪዝም ኢንቨስትመንቶች አማካሪ ፍሰሃ አስረስ፤ አመራሩ የዘርፉን አቅም በመረዳት በቁርጠኝነት መሥራቱን አድንቀዋል፡፡

የቱሪዝም ዘርፉ ከአምስቱ የኢኮኖሚ ምሰሶዎች አንዱ እንዲሆን መደረጉ ነባር መዳረሻዎችን ማደስን ጨምሮ በርካታ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎች መገንባታቸውን ገልጸዋል፡፡ 

የሱፐር ኦቫ ባለቤትና ኃላፊ ረድኤት ባዩ እንዳሉትም፤ መንግስት ተግባራዊ ያደረገው የሌማት ትሩፋት በርካታ ሰዎች ወደ ዘርፉ እንዲገቡ አድርጓል፡፡


 

ሱፐር ኦቫ አግሮቴክ የስጋ እና እንቁላል ጣይ ዶሮ አቅርቦትን ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ከውጭ ሀገራት ማስገባት መቻሉን ገልጸዋል፡፡

መንግስት ለሌማት ትሩፋት የሰጠው ትልቅ ትኩረት ፋብሪካዎችን ጨምሮ ስራቸውን እንዲያስፋፉ እና አዳዲሶቹም ወደ ዘርፉ እንዲሳቡ ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡

የከተማ ልማት ዘርፍ አማካሪ ኢንጂነር ዳዊት ኡርጌቾ በበኩላቸው፤ ቀደም ሲል ከከተማ አኳያ ተሽከርካሪ ተኮር የነበረ ዕቅድ መኖሩን አስታውሰው፤ አሁን ሰው ተኮር እንዲሆን መደረጉን ተናግረዋል፡፡


 

ሞተር አልባ የትራንስፖርት ስርዓቱን ወደ 50 በመቶ እንዲጠጋ የማድረግ ስርዓት መከተሉን ጠቁመው፤ በኮሪደር ልማቱም ለሞተር አልባ የትራንስፖርት ስርዓት ከፍተኛ ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡

አስተያየት ሰጪዎቹ ፤ የቱሪዝም መዳረሻ ልማቶች በስፋት መከናወናቸው ዘርፉ ለሀገር የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ከማሳደግ አኳያ ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ጠቁመዋል፡፡


 

የሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶች በዘመናዊ መልኩ እንዲመረቱ ብሎም ተደራሽነታቸው እንዲያድግ ማድረጉንም ገልጸዋል፡፡

በከተሞች እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ስራ ገጽታን ከመቀየር አኳያ ትልቅ ትርጉም ያመጣ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም