ቀጥታ፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ድህነትን ታሪክ ማድረግ እንደሚቻል ማሳያ ነው

ሰቆጣ፤ ጳጉሜን 4/2017(ኢዜአ)፡-ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በሕዝብ የላቀ ትብብር እውን መሆኑ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ከቆሙ ድህነትን ታሪክ ማድረግ እንደሚችሉ ማሳያ መሆኑን የሰቆጣ ነዋሪዎች ገለጹ።

በሰቆጣ ከተማ ኢዜአ  ያነጋገራቸው ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት የሕዳሴው  ግድብ ግንባታን በራስ አቅም ከፍጻሜ ማድረስ በመቻሉ  ታላቅ ኩራትና ደስታ እንደተሰማቸው  ተናግረዋል።

የዛሬ ብርሃን የነገ ሃገር ተረካቢ ትውልዶች ደግሞ የተሻለችና የበለፀገች ኢትዮጵያን ለማስረከብ በር የተከፈተበት ግዙፍ ፕሮጀክት መሆኑን  ገልጸዋል።  

አቶ ሃብቱ ይስሃቅ በሰቆጣ ከተማ በአትክልትና ፍራፍሬ ንግድ ስራ የተሰማሩ ሲሆን፤ የሕዳሴው ግድብ እውን እንዲሆን ቦንድ በመግዛት ሃገራዊ ሃላፊነታቸውን መወጣታቸውን አውስተዋል።


 

በአሁኑ ወቅት የሕዳሴው ግድብ በስኬት መጠናቀቁ እንዳስደሰታቸው ገልጸው፤በግድቡ መገንባት ሀገሪቱ  የገጠማትን ፈተናዎች ሁሉ በድል አድራጊነት መወጣት ችላለች ብለዋል። 

ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ከቆሙ የሃገርን ሰላም ከማፅናት ባለፈ ድሕነትን ታሪክ ማድረግ እንደሚችሉ ሕዳሴ ግድብ ትምሕርት የሚወሰድበት ፕሮጀክት እንደሆነ አንስተዋል።

ወይዘሮ አለሚቱ ደሴ በበኩላቸው፤  የሕዳሴው ግድብ የመሰረት ድንጋይ ከተጣለበት ጊዜ ጀምሮ የ10 ሺሕ ብር ቦንድ በመግዛት ለግድቡ እውን መሆን  የድርሻቸውን ሲወጡ እንደቆዩ ተናግረዋል።


 

አሁን ላይ የሕዳሴው ግድብ ግንባታ ተጠናቆ ለምረቃ በመድረሱ ደግሞ ታላቅ ኩራት እንደተሰማቸው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያዊያን ከተባበሩ ከሃገር ባለፈ ለአፍሪካ ኩራት የሚሆን ተግባር እንደሚፈፅሙ ሕዳሴ ግድብ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የሕዳሴው ግድብ እውን እንዲሆን ተማሪ እያለሁ ከ20 ብር  ጀምሮ አስተዋጽኦ ሳደርግ ቆይቻለው ያለው ደግሞ በከተማው ፀጉር በማስተካከል ስራ የተሰማራው ወጣት ሰፊው ወልደ ስላስ ነው።


 

የሕዳሴው ግድብ እውን ሆኖ ለስኬት መብቃቱ ደስታ እንደተሰማው ጠቅሶ፤ ሕዳሴ በቀጣይም የይቻላል መንፈስን ያላበሰና ድሕነትን በራስ አቅም ማሸነፍ እንደሚቻለ አሳይቷል ብሏል።

የሕዳሴው ግድብ እውን መሆን የሁሉም ኢትዮጵያዊያን  ኩራትና ደስታ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ወይዘሮ ተረፉ እማኙ ናቸው። 


 

የአካል ጉዳት ሳይገድበኝ ሰርቼ ከማገኘው ገቢ ቦንድ በመግዛት ለግድቡ ስኬታማነት የበኩሌን ሚና ተወጥቻለሁ፤ የሕዳሴው ግድብ እውን በመሆኑ ኩራት ተሰምቶኛል ሲሉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም