ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያን ማንሰራራት የሚያረጋግጡ ሥራዎች ተከናውነዋል - ኢዜአ አማርኛ
ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያን ማንሰራራት የሚያረጋግጡ ሥራዎች ተከናውነዋል
አዲስ አበባ፤ጳጉሜን 4/2017(ኢዜአ)፦ባለፉት ዓመታት በኃይል አቅርቦት፣ ለትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ እንዲሁም ለማዕድን ዘርፍ በተሰጠው ትኩረት የኢትዮጵያን ማንሰራራት የሚያረጋግጡ ሥራዎች መከናወናቸው ተገለጸ፡፡
ጳጉሜን 4 የማንሰራራት ቀን " ዘላቂ ልማት ለሀገራዊ ማንሰራራት " በሚል መሪ ሐሳብ በመላው ሀገሪቱ እየተከበረ ይገኛል፡፡
2017 በጀት ዓመት ኢትዮጵያ ከነበሩባት ማነቆዎች በመላቀቅ ታሪክ ቀያሪ ድሎችን ማስመዝገብ የጀመረችበት ዓመት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዓመቱ የማንሰራራት ዓመት ይሆናል ባሉት መሠረት የበጀት ዓመቱ ጉልህ ስኬቶች የተመዘገቡበት ብቻ ሳይሆን የማንሰራራት ጅማሮ የታየበት ሆኗል።
መንግሥት የጀመራቸው የብዝኃ ዘርፍ ኢኮኖሚ ዕሳቤዎች ውጤት ማምጣት የጀመሩበት፣ ለቀጣዩ የብልጽግና ጉዞ አስቻይ ተቋማት እና ሥርዓት የተፈጠረበት፣ ኢትዮጵያ ወደ ዓለም-አቀፋዊ ተወዳዳሪ የኢኮኖሚ ሥርዓት የገባችበት ጊዜም ነው፡፡
የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞ ከአዲስ አበባ - ጅቡቲ በሚጓዘው ባቡር ውስጥ የማንሰራራት ጉዞን በጉዞ በሚል መሪ ሐሳብ ውይይት ተካሂዷል፡፡
በውይይቱም ባለፈው ዓመት በታላቁ ህዳሴ ግድብ፣ በኢንዱስትሪ፣ በሌማት ትሩፋት፣ በአረንጓዴ አሻራ፣ በኮሪደር ልማት፣ በገበታ ለትውልድ እና በመደመር ትውልድ ፕሮጀክቶች የታዩ ውጤታማ ስራዎች የኢትዮጵያ የማንሰራራት ማሳያዎች ናቸው ተብሏል።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ተደራዳሪ ኢንጅነር ጌዲዮን አስፋው፤ ባለፉት ዓመታት በኢነርጂው ዘርፍ የተከናወኑ ውጤታማ ተግባራት አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ እንደገለጹት፤ በኢነርጂ ዘርፉ የኢትዮጵያን የቀጣይ ዘመን ጉዞ የሚተልሙ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡
የኢትዮጵያ ትልቅ የማንሰራራት ጉዞ ማሳያ የሆነው ታላቁ ህዳሴ ግድብ ከበርካታ ዓመታት ውጣ ውረድ በኋላ ተጠናቆ በዛሬው ዕለት ለምርቃት መብቃቱ ትልቅ ድል ነው ብለዋል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኃይል አቅርቦቱን በእጥፍ እንደሚያሳድግ ጠቁመው፤ ይህም ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋን ለማሳደግ ትልቅ እርምጃ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት በነፋስ፣ በጂኦተርማል እና በፀሐይ ኃይል አቅርቦት ውጤታማ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቁመው፤ በመጪው ጊዜም ይህ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ጭነት አመላላሾች እና ሺፒንግ ኤጀንትስ አሶሴሽን ፕሬዚዳንት ዳዊት ውብሸት፤ ባለፉት ዓመታት በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፍ ታሪክ ቀያሪ የሚባሉ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር መንገድ ባለፉት ዓመታት ከነበረበት ሳንካ በመውጣት በቴክኖሎጂ፣ በመሠረተ ልማት እና በሌሎች ዘርፎች ትልቅ ማንሰራራት ማሳየቱን ገልጸዋል፡፡
ወጭ ንግዱን ከማሳለጥ አኳያ አመርቂ ስራ መሥራት መጀመሩን ጠቁመው፤ በሳምንት ሁለት ጊዜ የነበረውን ምልልስ በቀን ወደ 10 ጊዜ ማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሀገር ኩራትነቱን እያስቀጠለ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ የኢትዮጵያ የመርከብ አገልግሎትም ወደ ማንሰራራት መሸጋገሩን አብራርተዋል፡፡
የኢቲ ሚኒራል ዴቨሎፕመንት አክሲዮን ማህበር ተወካይ ተሳታፊ ሽመልስ ፍሰሐ (ዶ/ር) በውይይቱ ወቅት እንደተናገሩት፤ መንግስት ለማዕድን ዘርፍ በሰጠው ትኩረት ውጤታማ ስራዎች እንዲከናወኑ አስችሏል፡፡
ድርጅታቸው 150 ቶን በሰዓት ማብላላት የሚችል የከሰል ማብላያ ፋብሪካ በመትከል ስራ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ይህ ፋብሪካ በመንግስት ፖሊሲ እና የህግ ድጋፍ ወደ ተግባር መግባቱን ጠቁመዋል፡፡
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ተደራዳሪ ኢንጅነር ጌዲዮን አስፋው እንዳሉት፤ መንግስት ለኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች እየሰጠ ያለው ትኩረት የአየር ንብረት ለውጥን ከመከላከል አኳያ ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በማዕድን ሚኒስቴር እየተተገበሩ የሚገኙ ውጤታማ ስራዎች በዘርፉ ትልቅ ለውጥ እንዲመጣ ማስቻሉንም ጠቁመዋል፡፡